መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ኦሪት ዘፍጥረት - Genesis

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50

1፤ ዮሴፍም የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘ። ዓይበታቸው የሚያነሣውን ያህል እህል ሙላላቸው፥ የሁሉንም ብር በየዓይበታቸው አፍ ጨምረው፤
2፤ በታናሹም ዓይበት አፍ የብሩን ጽዋዬንና የእህሉን ዋጋ ጨምረው። እርሱም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ።
3፤ ነግህ በሆነ ጊዜም ሰዎቹ አህዮቻቸውን ይዘው ይሄዱ ዘንድ ተሰናበቱ።
4፤ ከከተማይቱም ወጥተው ገና ሳይርቁ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ አለ። ተነሥተህ ሰዎቹን ተከተላቸው፤ በደረስህባቸውም ጊዜ እንዲህ በላቸው። በመልካሙ ፋንታ ስለ ምን ክፉን መለሳችሁ?
5፤ ጌታዬ የሚጠጣበት ምሥጢርንም የሚያውቅበት ጽዋ አይደለምን? ባደረጋችሁት ነገር በደላችሁ።
6፤ እርሱም ደርሰባቸው ይህንም ቃል ነገራቸው።
7፤ እነርሱም አሉት። ጌታዬ እንደዚህ ያለውን ቃል ለምን ይናገራል? ባሪያዎችህ ይህን ነገር የሚያደርጉ አይደሉም።
8፤ እነሆ፥ በዓይበታችን አፍ ያገኘነውን ብር ይዘን ከከነዓን አገር ወደ አንተ ተመልሰናል፤ ከጌታህ ቤት ወርቅ ወይስ ብር እንዴት እንሰርቃለን?
9፤ ከባሪያዎችህ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ይሙት፤ እኛም ደግሞ ለጌታችን ባሪያዎች እንሁን።
10፤ እርሱም አለ። አሁንም እንዲሁ እንደ ነገራችሁ ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ለእኔ ባሪያ ይሁነኝ፥ እናንተም ንጹሐን ትሆናላችሁ።
11፤ እየራሳቸውም ፈጥነው ዓይበታቸውን ወደ ምድር አወረዱ፥ እየራሳቸውም ዓይበታቸውን ፈቱ።
12፤ እርሱም ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በረበራቸው፥ ጽዋውንም በብንያም ዓይበት ውስጥ አገኘው።
13፤ ልብሳቸውንም ቀደዱ፥ ዓይበታቸውንም በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማይቱ ተመለሱ።
14፤ ይሁዳም ከወንድሞቹ ጋር ወደ ዮሴፍ ገባ፥ እርሱም ገና ከዚያው ነበረ፤ በፊቱም በምድር ላይ ወደቁ።
15፤ ዮሴፍም። ይህ ያደረጋችሁት ነገር ምንድር ነው? እንደ እኔ ያለ ሰው ምሥጢርን እንዲያውቅ አታውቁምን? አላቸው።
16፤ ይሁዳም አለ። ለጌታዬ ምን እንመልሳለን? ምንስ እንናገራለን? ወይስ በምን እንነጻለን? እግዚአብሔር የባሪያዎችህን ኃጢአት ገለጠ፤ እነሆ፥ እኛም ጽዋው ከእርሱ ዘንድ የተገኘበቱም ደግሞ ለጌታዬ ባሪያዎቹ ነን።
17፤ እርሱም እላቸው። ይህን አደርግ ዘንድ አይሆንልኝም፤ ጽዋው የተገኘበቱ ሰው እርሱ ባሪያ ይሁነኝ፤ እናንተም ወደ አባታችሁ በደኅና ውጡ።
18፤ ይሁዳም ወደ እርሱ ቀረበ እንዲህም አለ። ጌታዬ ሆይ፥ እኔ ባርያህ በጌታዬ ጆሮ አንዲት ቃልን እንድናገር እለምናለሁ፤ እኔንም ባሪያህን አትቆጣኝ፤ አንተ እንደ ፈርዖን ነህና።
19፤ ጌታዬ ባሪያዎቹን። አባት አላችሁን ወይስ ወንድም? ብሎ ጠየቀ።
20፤ እኛም ለጌታዬ እንዲህ አልነ። ሸማግሌ አባት አለን፥ በሽምግልናው የወለደውም ታናሽ ብላቴና አለ፤ ወንድሙም ሞተ፥ ከእናቱም እርሱ ብቻውን ቀረ፥ አባቱም ይወድደዋል።
21፤ አንተም ለባሪያዎችህ። ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም አየዋለሁ አልህ።
22፤ ጌታዬንም። ብላቴናው አባቱን መተው አይሆንለትም፤ የተወው እንደ ሆነ አባቱ ይሞታልና አልነው።
23፤ ባርያዎችህንም። ታናሽ ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም አልኽን።
24፤ ወደ ባርያህ ወደ አባታችን በተመለስን ጊዜም የጌታዬን ቃል ነገርነው።
25፤ አባታችንም። ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን አለ።
26፤ እኛም አልነው። እንሄድ ዘንድ አይሆንልንም፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ይወርድ እንደ ሆነ እኛም እንወርዳለን፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ከሌለ የዚያን ሰው ፊት ማየት አይቻለንምና።
27፤ ባሪያህ አባቴም እንዲህ አለን። ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆችን እንደ ወለደችልኝ እናንተ ታውቃላችሁ፤
28፤ አንዱም ከእኔ ወጣ። አውሬ በላው አላችሁኝ፥ እስከ ዛሬም አላየሁትም፤
29፤ ይህንም ከእኔ ለይታችሁ ደግሞ ብትወስዱት ክፋም ቢያገኘው፥ ሽበቴን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።
30፤ አሁንም እኔ ወደ አባቴ ወደ ባሪያህ ብሄድ፥ ብላቴናውም ከእኛ ጋር ከሌለ፥ ነፍሱ በብላቴናው ነፍስ ታስራለችና ብላቴናው ከእኛ ጋር እንደሌለ ባየ ጊዜ ይሞታል፤
31፤ ባሪያዎችህም የባሪያህን የአባታችንን ሽበት በኅዘን ወደ መቃብር ያወርዳሉ።
32፤ እኔ ባሪያህ በአባቴ ዘንድ ስለ ብላቴናው እንዲህ ብዬ ተውሼአለሁና። እርሱንስ ወደ አንተ ባላመጣው በአባቴ ዘንድ በዘመናት ሁሉ ኃጢአተኛ እሆናለሁ።
33፤ ስለዚህም እኔ ባሪያህ በጌታዬ ዘንድ ባሪያ ሆኜ በብላቴናው ፋንታ ልቀመጥ፤ ብላቴናውም ከወንድሞቹ ጋር ይውጣ።
34፤ አለዚያም ብላቴናው ከእኔ ጋር ከሌለ ወደ አባቴ እንዴት እወጣለሁ? አባቴን የሚያገኘውን መከራ እንዳላይ። a

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]