መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ኦሪት ዘሌዋውያን - Leviticus
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
15
16
17
18
19
20
21
22
23
24
25
26
27
1
፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2
፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ሰንበት ታድርግ።
3
፤ ስድስት ዓመት እርሻህን ዝራ፥ ስድስት ዓመትም ወይንህን ቍረጥ ፍሬዋንም አግባ።
4
፤ በሰባተኛው ዓመት ግን ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት፥ ለእግዚአብሔር ሰንበት፥ ትሁን፤ እርሻህን አትዝራ፥ ወይንህንም አትቍረጥ።
5
፤ የምድራችሁን የገቦ አትጨደው፥ ያልተቈረጠውንም የወይንህን ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን።
6
፤ የምድርም ሰንበት ለአንተ፥ ለወንድ ባሪያህም፥ ለሴት ባሪያህም፥ ለምንደኛውም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ይሁን።
7
፤ ለእንስሶችህም፥ በምድርህም ላሉት አራዊት ፍሬዋ ሁሉ መኖ ይሁን።
8
፤ ሰባት ጊዜ ሰባት አድርገህ የዓመታትን ሰንበት ሰባት ቍጠር፤ የሰባት ዓመታትም ሰንበት ዘመን አርባ ዘጠኝ ዓመት ትቈጥራለህ።
9
፤ ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን በቀንደ መለከት ታውጃለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃላችሁ።
10
፤ አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ።
11
፤ ያ አምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፥ የገቦውንም አትጨዱ፥ የወይኑንም ፍሬ አታከማቹ።
12
፤ ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ በሜዳ ላይ የበቀለውን ብሉ።
13
፤ በዚች በኢዮቤልዩ ዓመት ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ይመለሳል።
14
፤ ለባልንጀራህም አንዳች ብትሸጥለት፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ ሰው ባልንጀራውን አያታልል።
15
፤ ከኢዮቤልዩ በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይሸጥልሃል።
16
፤ እንደ ዓመታቱ ብዛት ዋጋውን ታበዛለህ፥ እንደ ዓመታቱም ማነስ ዋጋውን ታሳንሳለህ፤ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃል።
17
፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያታልል፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
18
፤ ሥርዓቴንም አድርጉ፥ ፍርዶቼንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ።
19
፤ ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ።
20
፤ እናንተም። ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን? ብትሉ፥
21
፤ እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች።
22
፤ በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ከአሮጌውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከአሮጌው እህል ትበላላችሁ።
23
፤ ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ጋር እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘላለም አትሽጡ።
24
፤ በርስታችሁም ምድር ሁሉ መቤዠትን ለምድሪቱ አድርጉ።
25
፤ ወንድምህም ቢደኸይ ከርስቱም ቢሸጥ፥ ለእርሱ የቀረበ ዘመዱ መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል።
26
፤ የሚቤዠውም ሰው ቢያጣ፥ እርሱም እጁ ቢረጥብ፥ ለመቤዠትም የሚበቃ ቢያገኝ፥
27
፤ የሽያጩን ዘመን ቈጥሮ የቀረውን ወደ ገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ።
28
፤ ለራሱም ዕዳውን መክፈል ባይችል፥ ሽያጩ በገዛው ሰው እጅ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቀመጥ፤ በኢዮቤልዩም ዓመት ይውጣ፥ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ።
29
፤ ሰውም ቅጥር ባለበት ከተማ መኖሪያ ቤትን ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ አንድ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ለመቤዠት ይችላል፤ ለአንድ ሙሉ ዓመት መቤዠት ይችላል።
30
፤ አንድ ዓመትም እስኪጨረስ ባይቤዠው፥ ቅጥር ባለበት ከተማ የሚሆን ቤት ለገዛው ለልጅ ልጁ ለዘላለም ይጸናለታል፤ በኢዮቤልዩም ከእርሱ አይወጣም።
31
፤ ቅጥር በሌለበት መንደር ያሉ ቤቶች ግን እንደ እርሻ ይቈጠራሉ፤ ይቤዣሉ፥ በኢዮቤልዩም ይወጣሉ።
32
፤ በእነርሱ ከተማ ያለ የሌዋውያን ቤት ግን ሌዋውያን ለዘላለም መቤዠት ይችላሉ።
33
፤ ማናቸውም ሰው ከሌዋውያን ቢገዛ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል የሌዋውያን ከተማ ቤቶች ርስቶቻቸው ናቸውና በርስቱ ከተማ ያለ የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ይመለሳል።
34
፤ በከተማቸውም ዙሪያ ያለችው መሰምርያ የዘላለም ርስታቸው ናትና አትሸጥም።
35
፤ ወንድምህ ቢደኸይ እጁም በአንተ ዘንድ ቢደክም፥ አጽናው፤ እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛም ከአንተ ጋር ይኑር።
36
፤ ወንድምህ ከአንተ ጋር ይኖር ዘንድ ከእርሱ ምንም ወለድ ወይም ትርፍ አትውሰድ፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
37
፤ ብርህን በወለድ አታበድረው፤ መኖህንም በትርፍ አትስጠው።
38
፤ የከነዓንን ምድር እሰጣችሁ ዘንድ፥ አምላክም እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
39
፤ ወንድምህም ቢደኸይ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፥ እንደ ባሪያ አድርገህ አትግዛው።
40
፤ እንደ ምንደኛና እንደ መጻተኛ ከአንተ ጋር ይሁን፤ እስከ ኢዮቤልዩም ዓመት ያገልግልህ።
41
፤ በዚያን ጊዜም እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ይውጣ፥ ወደ ወገኖቹም ወደ አባቱም ርስት ይመለስ።
42
፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸውና እንደ ባሪያዎች አይሸጡ።
43
፤ በጽኑ እጅ አትግዛው፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
44
፤ ወንድ ባሪያና ሴት ባሪያ መግዛት ብትፈልግ ግን በዙሪያችሁ ካሉት ከእነርሱ ከአሕዛብ ወንድና ሴት ባሪያዎችን ግዙ።
45
፤ ደግሞም በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት መጻተኞች፥ በምድራችሁም ውስጥ ከወለዱአቸው በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት ከዘራቸው ውስጥ ባሪያዎችን ግዙ፤ ርስትም ይሁኑላችሁ።
46
፤ ከእናንተም በኋላ ልጆቻችሁ ይወርሱአቸው ዘንድ ተዉአቸው፤ ከእነርሱም ባሪያዎችን ለዘላለም ትወስዳላችሁ፤ ነገር ግን የእስራኤልን ልጆች ወንድሞቻችሁን በጽኑ እጅ አትግዙአቸው።
47
፤ በአንተም ዘንድ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆን፥ ወንድምህም በእርሱ አጠገብ ቢደኸይ፥ ራሱንም ለመጻተኛው ወይም ለእንግዳው ወይም ለወገኖቹ ዘር ቢሸጥ፥
48
፤ ከተሸጠ በኋላ መቤዠት ይችላል፤ ከወንድሞቹ አንዱ ይቤዠው፤
49
፤ ወይም አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ይቤዠው፤ ወይም ከወገኑ ለእርሱ የቀረበ ዘመድ ይቤዠው፤ ወይም እርሱ እጁ ቢረጥብ ራሱን ይቤዠው።
50
፤ ከገዛውም ሰው ጋር ከገዛበት ዓመት ጀምሮ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቍጠር፤ የሽያጩም ብር እንደ ዓመታቱ ቍጥር ይሁን፤ እንደ ምንደኛውም ዘመን ከእርሱ ጋር ይሁን።
51
፤ ብዙ ዓመታትም ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቍጥር ከሽያጩ ብር የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ።
52
፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂቶች ዓመታት ቢቀሩ ከእርሱ ጋር ይቈጥራል፤ እንደ ዓመታቱም መጠንየመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ።
53
፤ በየዓመቱ እንደ ምንደኛ ከእርሱ ጋር ይኑር፤ በፊትህ በጽኑ እጅ አይግዛው።
54
፤ በዚህ ዘመን ሁሉ ግን ባይቤዥ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ይውጣ።
55
፤ የእስራኤል ልጆች ለእኔ ባሪያዎች ናቸውና፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]