መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
መጽሐፈ መሣፍንት - Judges
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
15
16
17
18
19
20
21
1
፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በምድያም እጅ ሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው።
2
፤ የምድያምም እጅ በእስራኤል ላይ ጠነከረች፤ ከምድያምም የተነሣ የእስራኤል ልጆች በተራራ ላይ ጕድጓድና ዋሻ ምሽግም አበጁ።
3
፤ እስራኤልም ዘር በዘሩ ጊዜ ምድያማውያን አማሌቃውያንም በምሥራቅም የሚኖሩ ሰዎች ይመጡባቸው ነበር፤
4
፤ በእነርሱም ላይ ይሰፍሩ ነበር፥ እስከ ጋዛም ድረስ የምድሩን ቡቃያ ያጠፉ ነበር፥ ምግብንም ለእስራኤል አይተዉም ነበር፤ በግ ወይም በሬ ወይም አህያ ቢሆን አይተዉም።
5
፤ እንስሶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው በብዛት እንደ አንበጣ ሆነው ይመጡ ነበር፤ ለእነርሱና ለግመሎቻቸውም ቍጥር አልነበራቸውም፤ ምድሪቱንም ያጠፉ ዘንድ ይመጡ ነበር።
6
፤ ከምድያምም የተነሣ እስራኤል እጅግ ተጠቁ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
7
፤ እንዲህም ሆነ፤ የእስራኤል ልጆች በምድያም ምክንያት ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥
8
፤ እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ልጆች ነቢይ ላከ፥ እርሱም አለ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፥ ከባርነትም ቤት አስለቀቅኋችሁ፤
9
፤ ከግብፃውያንም እጅ፥ ከሚጋፉአችሁም ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ፥ ከፊታችሁም አሳደድኋቸው፥ አገራቸውንም ሰጠኋችሁ፤
10
፤ እናንተንም። እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራያውያንን አማልክት አትፍሩ አልኋችሁ። እናንተ ግን ድምፄን አልሰማችሁም።
11
፤ የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው በአድባሩ ዛፍ በታች ተቀመጠ፤ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር።
12
፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ። አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው።
13
፤ ጌዴዎንም። ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ። እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው።
14
፤ እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው።
15
፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው።
16
፤ እግዚአብሔርም። በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው።
17
፤ እርሱም። በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ፥ የምትናገረኝም አንተ እንደ ሆንህ ምልክት አሳየኝ፤
18
፤ ወደ አንተም እስክመለስ ድረስ፥ ቍርባኔንም አምጥቼ እስካቀርብልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ከዚህ አትላወስ አለው። እርሱም። እስክትመለስ ድረስ እቆያለሁ አለ።
19
፤ ጌዴዎን ገባ የፍየሉንም ጠቦት የኢፍ መስፈሪያም ዱቄት የቂጣ እንጎቻ አዘጋጀ፤ ሥጋውን በሌማት አኖረ፥ መረቁንም በምንቸት ውስጥ አደረገ፥ ሁሉንም ይዞ በአድባሩ ዛፍ በታች አቀረበለት።
20
፤ የእግዚአብሔርም መልአክ። ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ ወስደህ በዚህ ድንጋይ ላይ አኑር፥ መረቁንም አፍስስ አለው። እንዲሁም አደረገ።
21
፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ ያለውን የበትሩን ጫፍ ዘርግቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ አስነካ፤ እሳትም ከድንጋዩ ውስጥ ወጥቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ በላ። የእግዚአብሔርም መልአክ ከዓይኑ ተሰወረ።
22
፤ ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ አየ፤ ጌዴዎንም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና አለ።
23
፤ እግዚአብሔርም። ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም አለው።
24
፤ ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም። እግዚአብሔር ሰላም ብሎ ጠራው። እርሱም እስከ ዛሬ ድረስ ለአቢዔዝራውያን በምትሆነው በዖፍራ አለ።
25
፤ እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት። የአባትህን በሬ፥ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን በሬ፥ ውሰድ፥ የአባትህ የሆነውንም የበኣል መሠዊያ አፍርስ፥ በእርሱም ዙሪያ ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቍረጥ፤
26
፤ በዚያም ኮረብታ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ አሳምረህ ሥራ ሁለተኛውንም በሬ ውሰድ፥ በዚያም በቈረጥኸው በማምለኪያ ዐፀዱ እንጨት ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርብ አለው።
27
፤ ጌዴዎንም ከባሪያዎቹ አሥር ሰዎችን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፤ የአባቱን ቤተ ሰቦች የከተማውንም ሰዎች ስለ ፈራ ይህን በቀን ለማድረግ አልቻለም፥ ነገር ግን በሌሊት አደረገው።
28
፤ የከተማውም ሰዎች ማልደው ተነሡ፥ እነሆም፥ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ፥ በዙሪያው ያለውም የማምለኪያ ዐፀድ ተቈርጦ፥ በተሠራውም መሠዊያ ላይ ሁለተኛው በሬ ተሠውቶ አገኙት።
29
፤ እርስ በርሳቸውም። ይህን ነገር ያደረገ ማን ነው? ተባባሉ። በጠየቁና በመረመሩም ጊዜ። ይህን ነገር ያደረገ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ነው አሉ።
30
፤ የከተማውም ሰዎች ኢዮአስን። የበኣልን መሠዊያ አፍርሶአልና፥ በዙሪያውም ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቈርጦአልና እንዲሞት ልጅህን አውጣ አሉት።
31
፤ ኢዮአስም እርሱን የተቃወሙትን ሁሉ። ለበኣል ትምዋገቱለታላችሁን? ወይስ እርሱን ታድናላችሁን? የሚምዋገትለት ሁሉ እስከ ነገ ይሙት፤ እርሱ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ካፈረሰው ጋር ለራሱ ይምዋገት አላቸው።
32
፤ ስለዚህም በዚያ ቀን። መሠዊያውን አፍርሶአልና በኣል ከእርሱ ጋር ይምዋገት ብሎ ጌዴዎንን። ይሩበኣል ብሎ ጠራው።
33
፤ ምድያማውያንም አማሌቃውያንም ሁሉ የምሥራቅም ሰዎች አንድ ሆነው ተሰበሰቡ፥ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ሰፈሩ።
34
፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በጌዴዎን ገባበት፥ እርሱም ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ የአቢዔዝርም ሰዎች ተጠርተው በኋላው ተከተሉት።
35
፤ ወደ ምናሴም ነገድ ሁሉ መልክተኞችን ሰደደ እነርሱም ደግሞ ተጠርተው በኋላው ተከተሉት፤ መልክተኞችንም ወደ አሴርና ወደ ዛብሎን ወደ ንፍታሌምም ሰደደ፥ እነርሱም ሊገናኙአቸው ወጡ።
36
፤ ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ ታድን እንደ ሆነ፥
37
፤ እነሆ፥ በአውድማው ላይ የተባዘተ የበግ ጠጕር አኖራለሁ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ጠል ቢሆን በምድሩም ሁሉ ደረቅ ቢሆን፥ እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ እንድታድናቸው አውቃለሁ አለ።
38
፤ እንዲሁም ሆነ፤ በነጋውም ማልዶ ተነሣ፥ ጠጕሩንም ጨመቀው፥ ከጠጕሩም የተጨመቀው ጠል ቆሬ ሙሉ ውኃ ሆነ።
39
፤ ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እኔ ይህን አንድ ጊዜ ስናገር አትቈጣኝ፤ እኔ ይህን አንድ ጊዜ በጠጕሩ፥ እባክህ፥ ልፈትን፤ አሁንም በጠጕሩ ብቻ ላይ ደረቅ ይሁን፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ይሁን አለው።
40
፤ እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት እንዲሁ አደረገ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ደረቅ ነበረ፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ነበረ። a
የገጽ ጫፍ
|
የሚቀጥለው ምዕራፍ
|
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]