መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

መጽሐፈ ሩት - Ruth

ምዕራፍ: 1 2 3 4

1፤ አማትዋም ኑኃሚን አለቻት። ልጄ ሆይ፥ መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈልግልሽምን?
2፤ አሁንም ከገረዶቹ ጋር የነበርሽበት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል።
3፤ እንግዲህ ታጠቢ፥ ተቀቢ፥ ልብስሽን ተላበሺ፥ ወደ አውድማውም ውረጂ፤ ነገር ግን መብሉንና መጠጡን እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታዪው።
4፤ በተኛም ጊዜ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም እግሩን ግለጪ፥ ተጋደሚም፤ የምታደርጊውንም እርሱ ይነግርሻል።
5፤ ሩትም። የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለቻት።
6፤ ወደ አውድማውም ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች።
7፤ ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፤ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች።
8፤ መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፤ እነሆም፥ አንዲት ሴት በእግርጌው ተኝታ ነበረች።
9፤ እርሱም። ማን ነሽ? አለ። እርስዋም። እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፤ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ አለችው።
10፤ ቦዔዝም አላት። ልጄ ሆይ፥ በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፤ ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት አድርገሻል።
11፤ አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ አትፍሪ፤ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ።
12፤ የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከእኔ የቀረበ ዘመድ አለ።
13፤ ዛሬ ሌሊት እደሪ፤ ነገም እርሱ ዋርሳ መሆን ቢወድድ መልካም ነው፥ ዋርሳ ይሁን፤ ዋርሳ ሊሆን ባይወድድ ግን፥ ሕያው እግዚአብሔርን እኔ ዋርሳ እሆንሻለሁ፤ እስኪነጋ ድረስ ተኚ።
14፤ እስኪነጋም በእግርጌው ተኛች፤ ቦዔዝም። ሴት ወደ አውድማው እንደ መጣች ማንም እንዳያውቅ ብሎ ነበርና ገና ሰውና ሰው ሳይተያይ ተነሣች።
15፤ እርሱም። የለበስሽውን ኩታ አምጥተሽ ያዢው አላት፤ በያዘችም ጊዜ ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፈረላት አሸከማትም።
16፤ እርሱም ወደ ከተማይቱ ሄደ። ወደ አማትዋም መጣች፥ አማትዋም። ልጄ ሆይ እንዴት ነሽ? አለቻት፤ እርስዋም ሰውዮው ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት።
17፤ ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ ብሎ ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ አለቻት።
18፤ እርስዋም። ልጄ ሆይ፥ ሰውዮው ይህን ነገር ዛሬ እስኪጨርስ ድረስ አያርፍምና ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ዝም በዪ አለች።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  |  መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]