መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ። - 2 Kings
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
15
16
17
18
19
20
21
22
23
24
25
1
፤ እንዲህም ሆነ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሊያወጣው በወደደ ጊዜ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ከጌልገላ ተነሣ።
2
፤ ኤልያስም ኤልሳዕን። እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቆይ አለው። ኤልሳዕም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ወደ ቤቴልም ወረዱ።
3
፤ በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ወጥተው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ አላቸው።
4
፤ ኤልያስም። ኤልሳዕ ሆይ፥ እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ።
5
፤ ወደ ኢያሪኮም መጡ። በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ ብሎ መለሰ።
6
፤ ኤልያስም። እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ሁለቱም ሄዱ።
7
፤ ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፥ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር።
8
፤ ኤልያስም መጐናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፥ ውኃውንም መታ፥ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ።
9
፤ ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን። ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን አለው፤ ኤልሳዕም። መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።
10
፤ እርሱም። አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም አለ።
11
፤ ሲሄዱም። እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።
12
፤ ኤልሳዕም አይቶ። አባቴ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች፥ ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ተረተረው።
13
፤ ከኤልያስም የወደቀውን መጐናጸፊያ አነሣ፥ ተመልሶም በዮርዳኖስ ዳር ቆመ።
14
፤ ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ ወስዶ ውኃውን መታና። የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? አለ፤ ውኃውንም በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ።
15
፤ ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ። የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር ተደፉ።
16
፤ እነርሱም። እነሆ፥ ከባሪያዎችህ ጋር አምሳ ኃያላን ሰዎች አሉ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደ አንድ ተራራ ወይም ወደ አንድ ሸለቆ ጥሎት እንደ ሆነ፥ ሄደው ጌታህን ይፈልጉት ዘንድ እንለምንሃለን አሉት። እርሱም። አትስደዱ አላቸው።
17
፤ እስኪያፍርም ድረስ ግድ ባሉት ጊዜ። ስደዱ አለ፤ አምሳም ሰዎች ሰደዱ፤ ሦስት ቀንም ፈልገው አላገኙትም።
18
፤ በኢያሪኮም ተቀምጦ ሳለ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም። አትሂዱ አላልኋችሁምን? አላቸው። v
19
፤ የከተማይቱም ሰዎች ኤልሳዕን። እነሆ፥ ጌታችን እንደምታይ የዚች ከተማ ኑሮ መልካም ነው፤ ውኃው ግን ክፉ ነው፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ትጨነግፋለች አሉት።
20
፤ እርሱም። አዲስ ማሰሮ አምጡልኝ፥ ጨውም ጨምሩበት አለ፤ ያንንም አመጡለት።
21
፤ ውኃው ወዳለበቱም ምንጭ ወጥቶ ጨው ጣለበትና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ውኃ ፈውሼዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ሞትና ጭንገፋ አይሆንበትም አለ።
22
፤ ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ነገር ውኃው እስከ ዛሬ ድረስ ተፈውሶአል።
23
፤ ከዚያም ወደ ቤቴል ወጣ፤ በመንገድም ሲወጣ ብላቴኖች ከከተማይቱ ወጥተው። አንተ መላጣ፥ ውጣ፤ አንተ መላጣ፥ ውጣ ብለው አፌዙበት።
24
፤ ዘወርም ብሎ አያቸው፥ በእግዚአብሔርም ስም ረገማቸው፤ ከዱርም ሁለት ድቦች ወጥተው ከብላቴኖች አርባ ሁለቱን ሰባበሩአቸው።
25
፤ ከዚያም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደ፥ ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]