መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

መጽሐፈ ምሳሌ - Proverbs

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31

1 ልጄ ሆይ፥ በክፉ ሰዎች አትቅና፥ ከእነርሱ ጋርም መሆንን አትውደድ፤
2 ልባቸው ግፍን ታስባለችና፥ ከንፈራቸውም ሽንገላን ትናገራለችና።
3 ቤት በጥበብ ይሠራል፥ በማስተዋልም ይጸናል።
4 በእውቀት ከከበረውና ካማረው ሀብት ሁሉ ጓዳዎች ይሞላሉ።
5 ጠቢብ ሰው ብርቱ ነው፥ አዋቂም ሰው ኃይሉን ያበዛል።
6 በመልካም ሥርዓት ሰልፍ ታደርጋለህ፤ ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው።
7 ጥበብ ለሰነፍ ከፍ ብላ የራቀች ናት፤ በበርም አፉን አይከፍትም።
8 ክፉ ለማድረግ የሚያስብ ተንኰለኛ ይባላል።
9 የስንፍና ሐሳብ ኃጢአት ነው፤ ሰዎች ፌዘኛውን ይጸየፉታል።
10 በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው።
11 ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፤ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን።
12 እነሆ፥ ይህን አላወቀውም ብትል፥ ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ነፍስህንም የሚመለከት እርሱ አያውቅምን? ለሰውስ ሁሉ እንደ ሥራው አይመልስለትምን?
13 ልጄ ሆይ፥ መልካም ነውና ማር ብላ፤ ወለላም ለጣምህ ጣፋጭ ነው።
14 ጥበብም ለነፍስህ እንዲሁ እንደሚሆን እወቅ፤ ብታገኘውም ፍጻሜህ መልካም ይሆናል፥ ተስፋህም አይጠፋም።
15 እንደ ኀጥእ በጻድቅ ቤት ላይ አትሸምቅ፤ ማደሪያውንም አታውክ።
16 ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፥ ይነሣማል፤ ኀጥኣን ግን በክፉ ላይ ይወድቃሉ።
17 ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥ በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ፥
18 እግዚአብሔር ያንን አይቶ በዓይኑ ክፉ እንዳይሆን፥ ቍጣውንም ከእርሱ እንዳይመልስ።
19 ስለ ኃጢአተኞች አትቈጣ፥ በክፉዎችም አትቅና።
20 ለኃጢአተኛ የፍጻሜ ተስፋ የለውምና፥ የኅጥኣንም መብራት ይጠፋልና።
21 ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔርንና ንጉሥን ፍራ፥ ከዓመፀኞችም ጋር አትደባለቅ።
22 መከራቸው ድንገት ይነሣልና፤ ከሁለቱ የሚመጣውን ጥፋት ማን ያውቃል? ፍን [የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።] የነገሩትን የሚሰማ ልጅ ከጥፋት የራቀ ነው፤ የነገሩትን የሚቀበልን ሰው እግዚአብሔር ይቀበለዋል። ከንጉሥ አንደበት ምንምን ሐሰት ይነገራል አይባልም፤ ከአንደበቱም የሚወጣ ሐሰት የለም። የንጉሥ ቃል ሾተል ናት፤ ለጥፋት የተሰጠችውን ሰው ሰውነት ታጠፋዋለች እንጂ አንድ አካል ብቻ የምታጠፋ አይደለም። ሰይፍ መዓቱ ብትሳል ግን ከወገኑ ጋር ሰውን ታጠፋለች፤ ከአሞሮች ግልገል ወገን የማይበላ እስኪሆን ድረስ እንደ እሳት ነበልባል ታቃጥላለች።
23 እነዚህ ደግሞ የጠቢባን ቃሎች ናቸው። በፍርድ ታደላ ዘንድ መልካም አይደለም።
24 ኀጥኡን። ጻድቅ ነህ የሚለውን ወገኖች ይረግሙታል አሕዛብም ይጠሉታል፤
25 የሚዘልፉት ግን ደስታ ይሆንላቸዋል፥ በላያቸውም መልካም በረከት ትመጣላቸዋለች።
26 በቀና ነገር የሚመልስ ከንፈርን ይስማል።
27 በስተ ሜዳ ሥራህን አሰናዳ፥ ስለ አንተ በእርሻ አዘጋጃት፤ ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ።
28 በባልንጀራህ ላይ በከንቱ ምስክር አትሁን፥ በከንፈርህም አታባብለው።
29 እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፥ እንደ ሥራውም እመልስበታለሁ አትበል።
30 በታካች ሰው እርሻ፥ አእምሮ በጐደለውም ሰው ወይን ቦታ አለፍሁ።
31 እነሆም፥ ሁሉ እሾህ ሞልቶበታል፥ ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል፥ የድንጋዩም ቅጥር ፈርሶአል።
32 ተመለከትሁና አሰብሁ፤ አየሁትና ተግሣጽን ተቀበልሁ።
33 ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂትም ታንቀላፋለህ፥ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፤
34 እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል። [በግዕዝ መጽሐፈ ተግሣጽ ይባላል]

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]