መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
መጽሐፈ መክብብ - Ecclesiastes
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
1
፤ ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል።
2
፤ ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና።
3
፤ ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና።
4
፤ የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው።
5
፤ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል።
6
፤ ከድስት በታች እንደሚቃጠል እሾህ ድምፅ የሰነፍ ሳቅ እንዲሁ ነው፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።
7
፤ ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል፤ ጉቦም ልቡን ያጠፋዋል።
8
፤ የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል፤ ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል።
9
፤ በነፍስህ ለቍጣ ችኩል አትሁን ቍጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና።
10
፤ ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና።
11
፤ ጥበብ ከርስት ጋር መልካም ነው፤ ፀሐይንም ለሚያዩ ሰዎች ትርፍን ይሰጣል።
12
፤ የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፤ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው።
13
፤ የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፤ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል?
14
፤ በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፤ በክፉም ቀን ተመልከት፤ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንም ያንም እንደዚያ ሠርቶአል።
15
፤ ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ ኀጥእም በክፋቱ እጅግ ዘመን ሲኖር፥ ይህን ሁሉ ከንቱ በሆነ ዘመኔ አየሁ።
16
፤ እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግ ጠቢብም አትሁን፥ እንዳትጠፋ።
17
፤ እጅግ ክፉ አትሁን፥ እልከኛም አትሁን፥ ጊዜህ ሳይደርስ እንዳትሞት።
18
፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሁሉ ይወጣልና ይህን ብትይዝ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው።
19
፤ በከተማ ከሚኖሩ ከአሥር ገዢዎች ይልቅ ጥበብ ጠቢብን ታበረታለች።
20
፤ በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና።
21
፤ ባሪያህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል፤
22
፤ አንተ ደግሞ ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና።
23
፤ ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንሁ፤ ጠቢብ እሆናለሁ አልሁ፥ እርስዋ ግን ከእኔ ራቀች።
24
፤ የሆነው ራቀ እጅግም ጠለቀ፤ መርምሮ የሚያገኘውስ ማን ነው?
25
፤ አውቅና እመረምር ዘንድ፥ ጥበብንና የነገሩን ሁሉ መደምደሚያ እፈልግ ዘንድ፥ ኃጢአትም ስንፍና፥ ስንፍናም እብደት እንደ ሆነች አውቅ ዘንድ እኔ በልቤ ዞርሁ።
26
፤ እኔም ከሞት ይልቅ የመረረ ነገር መርምሬ አገኘሁ፤ እርስዋም ልብዋ ወጥመድና መርበብ የሆነ፥ እጆችዋም እግር ብረት የሆኑ ሴት ናት፤ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነ ከእርስዋ ያመልጣል፥ ኃጢአተኛ ግን ይጠመድባታል።
27
፤ አንዱን በአንዱ ላይ ጨምሬ ወደ ነገሩ ሁሉ መደምደሚያ እደርስ ዘንድ፥ እነሆ፥ ይህን ነገር አገኘሁ ይላል ሰባኪው፤
28
፤ ነፍሴ እስከ ዛሬ ድረስ ትሻታለች፥ ነገር ግን አላገኘሁም፤ ከሺህ ወንዶች አንድ አገኘሁ፥ ከእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ሴት አላገኘሁም።
29
፤ እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው፥ እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፤ እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ።
የገጽ ጫፍ
|
የሚቀጥለው ምዕራፍ
|
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]