መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ትንቢተ ዳንኤል - Daniel

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12

1፤ በባቢሎን ንጉሥ በብልጣሶር በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በአልጋው ላይ ሕልምንና የራሱን ራእይ አየ፤ ከዚያም በኋላ ሕልሙን ጻፈ፥ ዋነኛውንም ነገር ተናገረ።
2፤ ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ። በሌሊት በራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በታላቁ ባሕር ላይ ይጋጩ ነበር።
3፤ አራትም ታላላቅ አራዊት ከባሕር ወጡ፥ እያንዳንዲቱም ልዩ ልዩ ነበረች።
4፤ መጀመሪያይቱ አንበሳ ትመስል ነበር፥ የንስርም ክንፍ ነበራት፤ ክንፎችዋም ከእርስዋ እስኪነቀሉ ድረስ አይ ነበር፥ ከምድርም ከፍ ከፍ ተደረገች፥ እንደ ሰውም በሁለት እግር እንድትቆም ተደረገች፥ የሰውም ልብ ተሰጣት።
5፤ እነሆም፥ ሁለተኛይቱ ድብ የምትመስል ሌላ አውሬ ነበረች፥ በአንድ ወገንም ቆመች፥ ሦስትም የጐድን አጥንቶች በአፍዋ ውስጥ በጥርስዋ መካከል ነበሩ፤ እንደዚህም። ተነሥተሽ እጅግ ሥጋ ብዪ ተባለላት።
6፤ ከዚህም በኋላ፥ እነሆ፥ ነብር የምትመስል በጀርባዋም ላይ አራት የወፍ ክንፎች የነበሩአት ሌላ አውሬ አየሁ፤ ለአውሬይቱም አራት ራሶች ነበሩአት፥ ግዛትም ተሰጣት።
7፤ ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፤ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፤ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፤ አሥር ቀንዶችም ነበሩአት።
8፤ ቀንዶችንም ተመለከትሁ፤ እነሆም፥ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፥ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ፤ እነሆም፥ በዚያ ቀንድ እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበሩበት።
9፤ ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፥ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ።
10፤ የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፤ ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፥ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ፍርድም ሆነ፥ መጻሕፍትም ተገለጡ።
11፤ የዚያን ጊዜም ቀንዱ ይናገረው ከነበረው ከታላቁ ቃል ድምፅ የተነሣ አየሁ፤ አውሬይቱም እስክትገደል፥ አካልዋም እስኪጠፋ ድረስ፥ በእሳትም ለመቃጠል እስክትሰጥ ድረስ አየሁ።
12፤ ከቀሩትም አራዊት ግዛታቸው ተወሰደ፤ የሕይወታቸው ዕድሜ ግን እስከ ዘመንና እስከ ጊዜ ድረስ ረዘመ።
13፤ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።
14፤ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።
15፤ በእኔም በዳንኤል በሥጋዬ ውስጥ መንፈሴ ደነገጠች፥ የራሴም ራእይ አስቸገረኝ።
16፤ በዚያም ከቆሙት ወደ አንዱ ቀርቤ ስለዚህ ሁሉ እውነቱን ጠየቅሁት፤ እርሱም ነገረኝ፥ የነገሩንም ፍቺ አስታወቀኝ።
17፤ እነዚህ አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ አራት ነገሥታት ናቸው።
18፤ ነገር ግን የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፥ እስከ ዘላለም ዓለምም መንግሥቱን ይወርሳሉ።
19፤ ከዚህም በኋላ ከቀሩት ሁሉ ተለይታ እጅግ ስለምታስፈራው፥ ጥርሶችዋም የብረት ጥፍሮችዋም የናስ ስለሆኑት፥ ስለምትበላውና ስለምታደቅቀው የቀረውንም በእግርዋ ስለምትረግጠው ስለ አራተኛይቱ አውሬ፥
20፤ በራስዋም ላይ ስለ ነበሩ ስለ አሥር ቀንዶች፥ በኋላም ስለ ወጣው፥ በፊቱም ሦስቱ ስለ ወደቁ፥ ዓይኖችና ትዕቢት የተናገረ አፍ ስለ ነበሩት፥ መልኩም ከሌሎች ስለ በለጠ ስለ ሌላው ቀንድ እውነቱን ለማወቅ ፈቀድሁ።
21፤ እነሆም፥ ያ ቀንድ ከቅዱሳን ጋር ሲዋጋ አየሁ፥
22፤ በዘመናት የሸመገለው እስኪመጣ ድረስ፥ ፍርድም ለልዑሉ ቅዱሳን እስኪሰጥ ድረስ፥ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወስዱበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ አሸነፋቸውም።
23፤ እንዲህም አለ። አራተኛይቱ አውሬ በምድር ላይ አራተኛ መንግሥት ትሆናለች፤ እርሱም ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፥ ምድሪቱንም ሁሉ ይበላል፥ ይረግጣታል ያደቅቃትማል።
24፤ አሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ አሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነርሱም በኋላ ሌላ ይነሣል፥ እርሱም ከፊተኞች የተለየ ይሆናል፥ ሦስቱንም ነገሥታት ያዋርዳል።
25፤ በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፥ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፥ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኵሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ።
26፤ ነገር ግን ፍርድ ይሆናል፥ እስከ ፍጻሜም ድረስ ያፈርሱትና ያጠፉት ዘንድ ግዛቱን ያስወግዱታል።
27፤ መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል፤ መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቶችም ሁሉ ይገዙለታል ይታዘዙለትማል።
28፤ የነገሩም ፍጻሜ እስከዚህ ድረስ ነው። እኔም ዳንኤል በአሳቤ እጅግ ተቸገርሁ፥ ፊቴም ተለወጠብኝ፤ ዳሩ ግን ነገሩን በልቤ ጠብቄአለሁ።

የገጽ ጫፍ  | የሚቀጥለው ምዕራፍ  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]