መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ትንቢተ ሆሴዕ - Hosea
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
1
፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድሩ ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለውና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
2
፤ እርግማንና ሐሰት ግዳይና ስርቆት ምንዝርናም ወጥተዋል፤ ደምም ወደ ደም ደርሶአል።
3
፤ ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርስዋም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር ይደክማሉ፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ።
4
፤ ነገር ግን ሕዝብህ ከካህን ጋር እንደሚከራከሩ ናቸውና ማንም አይከራከር፥ ማንም አይዝለፍ።
5
፤ በቀንም ትሰናከላለህ፥ ነቢዩም ከአንተ ጋር በሌሊት ይሰናከላል፤ እናትህንም አጠፋታለሁ።
6
፤ ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ።
7
፤ እንደ ብዛታቸው መጠን ኃጢአት ሠሩብኝ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ነውር እለውጣለሁ።
8
፤ የሕዝቤም ኃጢአት መብል ሆኖላቸዋል፥ ልባቸውንም ወደ በደላቸው አድርገዋል።
9
፤ እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፤ በመንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፥ ሥራቸውንም እመልስባቸዋለሁ።
10
፤ እግዚአብሔርንም መጠበቅ ትተዋልና ሲበሉ አይጠግቡም፥ ሲያመነዝሩም አይበዙም።
11
፤ ግልሙትናና የወይን ጠጅ ስካርም አእምሮን ያጠፋል።
12
፤ የግልሙትና መንፈስ ሕዝቤን አስቶአቸዋልና፥ እነርሱም ከአምላካቸው ርቀው አመንዝረዋልና በትራቸውን ይጠይቃሉ፥ ዘንጋቸውም ይመልስላቸዋል።
13
፤ በተራሮችም ራስ ላይ ይሠዋሉ፤ ጥላውም መልካም ነውና ከኮምበልና ከልብን ከአሆማም ዛፍ በታች በኮረብቶች ላይ ያጥናሉ፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ይገለሙታሉ፥ ሙሽሮቻችሁም ያመነዝራሉ።
14
፤ ወንዶችም ደግሞ ከጋለሞቶች ጋር ይጫወታሉና፥ ከጋለሞቶችም ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ በገለሞቱ ጊዜ፥ ሙሽሮቻችሁም ባመነዘሩ ጊዜ አልቀጣቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ይገለበጣል።
15
፤ እስራኤል ሆይ፥ አንተ ብታመነዝር ይሁዳ አይበድል፤ እናንተም ወደ ጌልገላ አትግቡ፥ ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፥ ወይም። ሕያው እግዚአብሔርን! ብላችሁ አትማሉ።
16
፤ እስራኤል እንደ እልከኛ ጊደር እንቢ ብሎአል፤ እግዚአብሔርስ በሰፊው ቦታ እንደ ጠቦት ያሰማራዋልን?
17
፤ ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጋጠመ፤ ተወው።
18
፤ ስካርን ፈጽመዋል፥ ግልሙትናንም አብዝተዋል፤ አለቆችዋም ነውርን እጅግ ወደዱ።
19
፤ ነፋስ በክንፍዋ አስሮአታል፤ ከመሥዋዕታቸውም የተነሣ ያፍራሉ።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]