መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ትንቢተ አሞጽ - Amos
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
1
፤ ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ። መድረኮቹ ይናወጡ ዘንድ ጕልላቶቹን ምታ፥ በራሳቸውም ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም።
2
፤ ወደ ሲኦል ቢወርዱ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይም ቢወጡ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤
3
፤ በቀርሜሎስም ራስ ውስጥ ቢሸሸጉ ፈልጌ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ ከዓይኔ ቢደበቁ ከዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል፤
4
፤ በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ ከዚያ ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል፤ ዓይኔንም በእነርሱ ላይ ለክፋት እንጂ ለመልካም አላደርግም።
5
፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድርን ይዳስሳል እርስዋም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ሙላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች፥ ደግሞ እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች።
6
፤ አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው።
7
፤ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?
8
፤ እነሆ፥ የጌታ የእግዚአብሔር ዓይኖች በኃጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፥ ከምድርም ፊት አጠፋታለሁ፤ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፥ ይላል እግዚአብሔር።
9
፤ እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ እህልም በወንፊት እንዲነፋ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እነፋለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም።
10
፤ ክፉው ነገር አይደርስብንም፥ አያገኘንምም የሚሉ የሕዝቤ ኃጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ።
11
፤ በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤
12
፤ ይኸውም የኤዶምያስን ቅሬታ፥ ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ ይወርሱ ዘንድ ነው፥ ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር።
13
፤ እነሆ፥ አራሹ አጫጁን፥ ወይን ጠማቂውም ዘሪውን የሚያገኝበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ተራሮችም በተሀውን የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይቀልጣሉ።
14
፤ የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፤ አታክልትንም ያባጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ።
15
፤ በምድራቸውም እተክላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም፥ ይላል አምላክህ እግዚአብሔር
የገጽ ጫፍ
|
የሚቀጥለው ምዕራፍ
|
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]