መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ትንቢተ ሶፎንያስ - Zephaniah

ምዕራፍ: 1 2 3

1፤ ለዓመፀኛይቱና ለረከሰች ለአስጨናቂይቱም ከተማ ወዮላት!
2፤ ድምፅን አልሰማችም፥ ተግሣጽንም አልተቀበለችም፤ በእግዚአብሔርም አልታመነችም፥ ወደ አምላክዋም አልቀረበችም።
3፤ በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ እንደሚያገሡ አንበሶች ናቸው፤ ፈራጆችዋም እስከ ነገ ድረስ ምንም እንደማያስቀሩ እንደ ማታ ተኵላዎች ናቸው።
4፤ ነቢያቶችዋ ቅሌታሞችና ተንኰለኞች ሰዎች ናቸው፤ ካህናቶችዋም መቅደሱን አርክሰዋል፥ በሕግም ላይ ግፍ ሠርተዋል።
5፤ እግዚአብሔር በውስጥዋ ጻድቅ ነው፤ ክፋትን አያደርግም፤ ፍርዱን በየማለዳው ወደ ብርሃን ያወጣል፥ ሳያወጣውም አይቀርም፤ ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም።
6፤ አሕዛብን አጥፍቻለሁ፤ ግንቦቻቸው ሁሉ ፈርሰዋል፤ መንገዳቸውን ማንም እንዳያልፍባት ምድረ በዳ አድርጌአለሁ፥ ከተሞቻቸውም ማንም እንዳይኖርባቸው፥ አንድስ እንኳ እንዳይቀመጥባቸው ፈርሰዋል።
7፤ እኔም- ይፈሩኛል፥ ተግሣጽንም ይቀበላሉ፤ ካዘዝኋትም ሁሉ ከዓይንዋ ምንም አይጠፋም ብዬ ነበር፤ እነርሱ ግን በማለዳ ተነሥተው ድርጊታቸውን ሁሉ አረከሱ።
8፤ መዓቴንና የቍጣዬን ትኵሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፥ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና፥ ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።
9፤ በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሐን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።
10፤ ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቍርባኔን ያመጡልኛል።
11፤ በዚያን ጊዜ እየታበዩ የሚፎክሩትን ከመካከልሽ አወጣለሁና፥ አንቺም በቅዱስ ተራራዬ ዳግመኛ አትኰሪምና በዚያ ቀን በእኔ ላይ ተላልፈሽ በሠራሽው ሥራ ሁሉ አትፍሪም።
12፤ በመካከልሽም የዋህና ትሑት ሕዝብን አስቀራለሁ፤ በእግዚአብሔርም ስም ይታመናሉ።
13፤ የእስራኤል ቅሬታ ኃጢአትን አይሠሩም፥ ሐሰትንም አይናገሩም፥ በአፋቸውም ውስጥ ተንኰለኛ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፥ ይመሰጉማል፥ የሚያስፈራቸውም የለም።
14፤ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፥ እልል በል፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሤት አድርጊ ደስም ይበልሽ።
15፤ እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፥ ጠላትሽንም ጥሎአል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም።
16፤ በዚያን ቀን ለኢየሩሳሌም። ጽዮን ሆይ፥ አትፍሪ፥ እጆችሽም አይዛሉ።
17፤ አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፤ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል ይባላል።
18፤ ከጉባኤው ርቀው የሚያዝኑትን፥ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፤ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር።
19፤ በዚያ ዘመን እነሆ፥ ባስጨነቁሽ ሁሉ ላይ አደርግባቸዋለሁ፤ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፤ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ።
20፤ በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  |  መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]