መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ትንቢተ ሚልክያ - Malachi
ምዕራፍ:
1
2
3
4
1
፤ አሁንም እናንተ ካህናት ሆይ፥ ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።
2
፤ ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፥ በልባችሁም ባታደርጉት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እርግማን እሰድድባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማታለሁ፤ አሁንም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና እኔ ረግሜአታለሁ።
3
፤ እነሆ፥ ክንዳችሁን እገሥጻለሁ፥ የመሥዋዕታችሁንም ፋንድያ በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ ከእርሱም ጋር በአንድነት ትወሰዳላችሁ።
4
፤ ቃል ኪዳኔ ከሌዊ ጋር ይሆን ዘንድ ይህን ትእዛዝ እንደ ሰደድሁላችሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
5
፤ ቃል ኪዳኔ ከእርሱ ጋር የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነበረ፤ ይፈራ ዘንድም እነርሱን ሰጠሁት፤ እርሱም ፈራኝ፥ ከስሜም የተነሣ ደነገጠ።
6
፤ የእውነት ሕግ በአፉ ውስጥ ነበረች፥ በከንፈሩም ውስጥ በደል አልተገኘበትም፤ ከእኔም ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፥ ብዙ ሰዎችንም ከኃጢአት መለሰ።
7
፤ ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፥ ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል።
8
፤ እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል፤ በሕግም ብዙ ሰዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አስነውራችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
9
፤ ስለዚህ መንገዴን እንዳልጠበቃችሁ፥ በሕግም ለሰው ፊት እንዳዳላችሁ መጠን፥ እኔ ደግሞ በሕዝብ ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ አድርጌአችኋለሁ።
10
፤ ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን? የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማስነቀፍ እኛ እያንዳንዳችን ወንድማችንን ስለ ምን አታለልን?
11
፤ እግዚአብሔር የወደደውን መቅደስ ይሁዳ አርክሶአልና፥ የእንግዳውንም አምላክ ልጅ ሚስት አድርጎ አግብቶአልና ይሁዳ አታልሎአል፥ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም ውስጥ ርኵሰት ተሠርቶአል።
12
፤ ይህን ከሚያደርግ ሰው፥ እግዚአብሔር የሚጠራውንና የሚመልሰውን ለሠራዊትም ጌታ ለእግዚአብሔር ቍርባን የሚያቀርበውን ከያዕቆብ ድንኳን ያጠፋል።
13
፤ ይህንም ደግሞ አድርጋችኋል፤ እግዚአብሔር ቍርባኑን ዳግመኛ እንዳይመለከት፥ ከእጃችሁም በደስታ እንዳይቀበለው መሠዊያውን በእንባና በልቅሶ በኀዘንም ትከድናላችሁ።
14
፤ እናንተም። ስለ ምንድር ነው? ብላችኋል። ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታልለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው።
15
፤ እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድር ነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል።
16
፤ መፋታትን እጠላለሁ፥ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፥ ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ።
17
፤ እግዚአብሔርን በቃላችሁ አታክታችኋል። እናንተም። ያታከትነው በምንድር ነው? ብላችኋል። ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው፥ እርሱም በእነርሱ ደስ ይለዋል፤ ወይስ። የፍርድ አምላክ ወዴት አለ? በማለታችሁ ነው።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]