መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

የዮሐንስ ወንጌል - John

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21
Audio  

1 ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አየ።
2 ደቀ መዛሙርቱም። መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው ጠየቁት።
3 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ። የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም።
4 ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች።
5 በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ።
6 ይህን ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና።
7 ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው፤ ትርጓሜው የተላከ ነው። ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም መጣ።
8 ጐረቤቶቹም ቀድሞም ሲለምን አይተውት የነበሩ። ይህ ተቀምጦ ይለምን የነበረ አይደለምን? አሉ።
9 ሌሎች። እርሱ ነው አሉ፤ ሌሎች። አይደለም እርሱን ይመስላል እንጂ አሉ፤ እርሱ። እኔ ነኝ አለ። 10 ታድያ። ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ? አሉት። 11 እርሱ መልሶ። ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ አድርጎ አይኖቼን ቀባና። ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ አለኝ፤ ሄጄ ታጥቤም አየሁ አለ። 12 ያ ሰው ወዴት ነው? አሉት። አላውቅም አለ። 13 በፊት ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። 14 ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዓይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበረ። 15 ስለዚህ ፈሪሳውያን ደግሞ እንዴት እንዳየ እንደ ገና ጠየቁት። እርሱም። ጭቃ በዓይኖቼ አኖረ ታጠብሁም አያለሁም አላቸው። 16 ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ። ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም አሉ። ሌሎች ግን። ኃጢአትኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች ሊያደርግ እንዴት ይችላል? አሉ። 17 በመካከላቸውም መለያየት ሆነ። ከዚህም የተነሣ ዕውሩን። አንተ ዓይኖችህን ስለ ከፈተ ስለ እርሱ ምን ትላለህ? ደግሞ አሉት። እርሱም። ነቢይ ነው አለ። 18 አይሁድ የዚያን ያየውን ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ ዕውር እንደ ነበረ እንዳየም ስለ እርሱ አላመኑም፥ 19 እነርሱንም። እናንተ ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል? ብለው ጠየቁአቸው።
20 ወላጆቹም መልሰው። ይህ ልጃችን እንደ ሆነ ዕውርም ሆኖ እንደ ተወለደ አናውቃለን፤
21 ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም፥ ወይም ዓይኖቹን ማን እንደ ከፈተ እኛ አናውቅም፤ ጠይቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ ራሱ ይናገራል አሉ።
22 ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህን አሉ፤ እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና።
23 ስለዚህ ወላጆቹ። ሙሉ ሰው ነው፥ ጠይቁት አሉ።
24 ስለዚህ ዕውር የነበረውን ሰው ሁለተኛ ጠርተው። እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን አሉት።
25 እርሱም መልሶ። ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ አለ።
26 ደግመውም። ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ? አሉት።
27 እርሱም መልሶ። አስቀድሜ ነገርኋችሁ አልሰማችሁምም፤ ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን? አላቸው።
28 ተሳድበውም። አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፥ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤
29 እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፥ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት።
30 ሰውዬው መለሰ እንዲህም አላቸው። ከወዴት እንደ ሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፥ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ።
31 እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን።
32 ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤
33 ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር።
34 መልሰው። አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወለድህ፥ አንተም እኛን ታስተምረናለህን? አሉት። ወደ ውጭም አወጡት።
35 ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ሲያገኘውም። አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው።
36 እርሱም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ።
37 ኢየሱስም። አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው።
38 እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም።
39 ኢየሱስም። የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ አለ።
40 ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሰምተው። እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን? አሉት።
41 ኢየሱስም አላቸው። ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን። እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል።

የገጽ ጫፍ  | የሚቀጥለው ምዕራፍ  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]