መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

የሐዋርያት ሥራ - Acts

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28

1 ከዚህም በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ መጣ።
2 በወገኑም የጳንጦስ ሰው የሚሆን አቂላ የሚሉትን አንድ አይሁዳዊ አገኘ፤ እርሱም ከጥቂት ጊዜ በፊት ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር ከኢጣልያ መጥቶ ነበር፥ አይሁድ ከሮሜ ይወጡ ዘንድ ቀላውዴዎስ አዞ ነበርና፤ ወደ እነርሱ ቀረበ፥
3 ሥራቸውም አንድ ስለ ነበረ በእነርሱ ዘንድ ተቀምጦ በአንድ ላይ ሠሩ፤ ሥራቸው ድንኳን መስፋት ነበረና።
4 በየሰንበቱም ሁሉ በምኵራብ ይነጋገር ነበር፥ አይሁድንና የግሪክንም ሰዎች ያስረዳ ነበር።
5 ሲላስና ጢሞቴዎስም ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ፥ ጳውሎስ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ለቃሉ ይተጋ ነበር።
6 ነገር ግን በተቃወሙትና በተሳደቡ ጊዜ፥ ልብሱን እያራገፈ። ደማችሁ በራሳችሁ ነው፤ እኔ ንጹሕ ነኝ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ አላቸው።
7 ከዚያም ወጥቶ ኢዮስጦስ ወደሚባል እግዚአብሔርን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ገባ ቤቱም በምኩራብ አጠገብ ነበረ።
8 የምኵራብ አለቃ ቀርስጶስም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፥ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙ በሰሙ ጊዜ አምነው ተጠመቁ።
9-
10 ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን። እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው።
11 በመካከላቸውም የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር ተቀመጠ።
12 ጋልዮስም በአካይያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ፥ አይሁድ በአንድ ልብ ሆነው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፥ ወደ ፍርድ ወንበርም አምጥተው።
13 ይህ ሕግን ተቃውሞ እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ ሰዎችን ያባብላል አሉ።
14 ጳውሎስም አፉን ሊከፍት ባሰበ ጊዜ፥ ጋልዮስ አይሁድን። አይሁድ ሆይ፥ ዓመፅ ወይም ክፉ በደል በሆነ እንድታገሣችሁ በተገባኝ፤
15 ስለ ቃልና ስለ ስሞች ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን፥ ራሳችሁ ተጠንቀቁ እኔ በዚህ ነገር ፈራጅ እሆን ዘንድ አልፈቅድምና አላቸው።
16 ከፍርድ ወንበርም ፊት አስወጣቸው።
17 የግሪክ ሰዎችም ሁሉ የምኩራብ አለቃ ሶስቴንስን ይዘው በወንበሩ ፊት መቱት፤ በእነዚህም ነገሮች ጋልዮስ ግድ የለውም ነበር።
18 ከዚህም በኋላ ጳውሎስ እጅግ ቀን ተቀምጦ ወንድሞቹንም ተሰናብቶ በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ፤ ስለትም ነበረበትና ራሱን በክንክራኦስ ተላጨ፤ ጵርስቅላና አቂላም ከእርሱ ጋር ነበሩ።
19 ወደ ኤፌሶንም በደረሱ ጊዜ እነዚያን ከዚያ ተዋቸው፥ ራሱ ግን ወደ ምኵራብ ገብቶ ከአይሁድ ጋር ይነጋገር ነበር።
20 እነርሱም ብዙ ጊዜ እንዲቀመጥላቸው ሲለምኑት እሺ አላለም፤
21 ነገር ግን ሲሰናበታቸው። የሚመጣውን በዓል በኢየሩሳሌም አደርግ ዘንድ ይገባኛል እግዚአብሔር ቢፈቅድ ግን ወደ እናንተ ደግሞ እመለሳለሁ አላቸው። ከኤፌሶንም በመርከብ ተነሣ።
22 ወደ ቂሣርያም በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ።
23 ጥቂት ቀንም ቆይቶ ወጣ፥ ደቀ መዛሙርትንም ሁሉ እያጸና በገላትያ አገርና በፍርግያ በተራ አለፈ።
24 በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ።
25 እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፥ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር።
26 እርሱም በምኵራብ ገልጦ ይናገር ጀመር። ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ፥ ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት።
27 እርሱም ወደ አካይያ ማለፍ በፈቀደ ጊዜ፥ ወንድሞቹ አጸናኑት፥ ይቀበሉትም ዘንድ ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት፤ በደረሰም ጊዜ አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ ይጠቅማቸው ነበር፤
28 ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ነበርና።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]