መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ወደ ሮሜ ሰዎች - Romans

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16

1 እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም።
2 ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን?
3 ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?
4 እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን።
5 ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤
6 ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና።
7-8 ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን፤
9 ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ፊት እንዳይሞት ሞትም ወደ ፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና።
10 መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቶአልና፤ በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሔር ይኖራል።
11 እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቈጠሩ።
12 እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤
13 ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
14 ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና።
15 እንግዲህ ምን ይሁን? ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢአትን እንሥራን? አይደለም።
16 ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፥ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ።
17-
18 ነገር ግን አስቀድማችሁ የኃጢአት ባሪያዎች ከሆናችሁ፥ ለተሰጣችሁለት ለትምህርት ዓይነት ከልባችሁ ስለ ታዘዛችሁ፥ ከኃጢአትም አርነት ወጥታችሁ ለጽድቅ ስለ ተገዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
19 ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ።
20 የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና።
21 እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና።
22 አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው።
23 የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።

የገጽ ጫፍ  | የሚቀጥለው ምዕራፍ  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]