መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ኦሪት ዘኍልቍ - Numbers

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፥ ከእነርሱም ከእያንዳንዱ ከየአባቶቻቸው ቤት አንድ አንድ በትር፥ ከአለቆቻቸው ከየአባቶቻቸው ቤት አሥራ ሁለት በትሮች፥ ውሰድ፤ የእያንዳንዱንም ስም በየበትሩ ላይ ጻፍ።
3፤ አንድ በትርም ለአባቶቻቸው ቤት አለቃ ይሆናልና በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ።
4፤ እኔ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት አኑራቸው።
5፤ እንዲህም ይሆናል፤ የመረጥሁት ሰው በትር ታቈጠቁጣለች፤ በእናንተም ላይ የሚያጕረመርሙባችሁን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ።
6፤ ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ አለቆቻቸው ሁሉ አሥራ ሁለት በትሮች፥ እያንዳንዱም አለቃ በየአባቱ ቤት አንድ አንድ በትር፥ ሰጡት፤ የአሮንም በትር በበትሮቻቸው መካከል ነበረች።
7፤ ሙሴም በትሮቹን በእግዚአብሔር ፊት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ አኖራቸው።
8፤ እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ፤ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቈጠቈጠች፥ ለመለመችም፥ አበባም አወጣች፥ የበሰለ ለውዝም አፈራች።
9፤ ሙሴም በትሮችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አወጣቸው፤ እነርሱም አዩ፥ እያንዳንዱም በትሩን ወሰደ።
10፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የአሮንን በትር ወደ ምስክሩ ፊት መልስ፤ ማጕረምረማቸው ከእኔ ዘንድ እንዲጠፋ እነርሱም እንዳይሞቱ ለሚያምፁብኝ ልጆች ምልክት ሆና ትጠበቅ አለው።
11፤ ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።
12፤ የእስራኤልም ልጆች ሙሴን።እነሆ፥ እንሞታለን፥ እንጠፋለን፥ ሁላችንም እንጠፋለን።
13፤ የሚቀርብ ሁሉ፥ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ የሚቀርብ፥ ይሞታል፤ በውኑ ሁላችን እንሞታለንን? ብለው ተናገሩት።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]