መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ኦሪት ዘኍልቍ - Numbers

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36

1፤ የእስራኤልም ልጆች ጕዞ ከሙሴና ከአሮን እጅ በታች በጭፍሮቻቸው ከግብፅ በወጡ ጊዜ እንዲህ ነበረ።
2፤ ሙሴም በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ጕዞአቸው አወጣጣቸውን ጻፈ፤ እንደ አወጣጣቸውም ጕዞአቸው እንዲህ ነበረ።
3፤ በመጀመሪያው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን ከራምሴ ተጓዙ፤ ከፋሲካ በኋላ በነጋው የእስራኤል ልጆች ግብፃውያን ሁሉ እያዩ ከፍ ባለች እጅ ወጡ።
4፤ በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው።
5፤ የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተጕዘው በሱኮት ሰፈሩ።
6፤ ከሱኮትም ተጕዘው በምድረ በዳ ዳርቻ ባለች በኤታም ሰፈሩ።
7፤ ከኤታምም ተጕዘው በበኣልዛፎን ፊት ወደ ነበረች ወደ ፊሀሒሮት ተመለሱ፤ በሚግዶልም ፊት ለፊት ሰፈሩ።
8፤ ከፊሀሒሮትም ተጕዘው በባሕሩ ውስጥ ወደ ምድረ በዳ አለፉ፤ በኤታምም በረሀ የሦስት ቀን መንገድ ሄደው በማራ ሰፈሩ።
9፤ ከማራም ተጕዘው ወደ ኤሊም መጡ፤ በኤሊምም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮች ሰባ ዘንባቦችም ነበሩ፤ በዚያም ሰፈሩ።
10፤ ከኤሊምም ተጕዘው በኤርትራ ባሕር ዳር ሰፈሩ።
11፤ ከኤርትራም ባሕር ተጕዘው በሲን ምድረ በዳ ሰፈሩ።
12፤ ከሲን ምድረ በዳም ተጕዘው በራፋቃ ሰፈሩ።
13፤ ከራፋቃም ተጕዘው በኤሉስ ሰፈሩ።
14፤ ከኤሉስም ተጕዘው በራፊዲም ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም።
15፤ ከራፊዲምም ተጕዘው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ።
16፤ ከሲናም ምድረ በዳ ተጕዘው በምኞት መቃብር ሰፈሩ።
17፤ ከምኞት መቃብርም ተጕዘው በሐጼሮት ሰፈሩ።
18፤ ከሐጼሮትም ተጕዘው በሪትማ ሰፈሩ።
19፤ ከሪትማም ተጕዘው በሬሞን ዘፋሬስ ሰፈሩ።
20፤ ከሬሞን ዘፋሬስም ተጕዘው በልብና ሰፈሩ።
21፤ ከልብናም ተጕዘው በሪሳ ሰፈሩ።
22፤ ከሪሳም ተጕዘው በቀሄላታ ሰፈሩ።
23፤ ከቀሄላታም ተጕዘው በሻፍር ተራራ ሰፈሩ።
24፤ ከሻፍር ተራራም ተጕዘው በሐራዳ ሰፈሩ።
25፤ ከሐራዳም ተጕዘው በመቅሄሎት ሰፈሩ።
26፤ ከመቅሄሎትም ተጕዘው በታሐት ሰፈሩ።
27፤ ከታሐትም ተጕዘው በታራ ሰፈሩ።
28፤ ከታራም ተጕዘው በሚትቃ ሰፈሩ።
29፤ ከሚትቃም ተጕዘው በሐሽሞና ሰፈሩ።
30፤ ከሐሽሞናም ተጕዘው በሞሴሮት ሰፈሩ።
31፤ ከሞሴሮትም ተጕዘው በብኔያዕቃን ሰፈሩ።
32፤ ከብኔያዕቃንም ተጕዘው በሖርሃጊድጋድ ሰፈሩ።
33፤ ከሖርሃጊድጋድም ተጕዘው በዮጥባታ ሰፈሩ።
34፤ ከዮጥባታም ተጕዘው በዔብሮና ሰፈሩ።
35፤ ከዔብሮናም ተጕዘው በዔጽዮንጋብር ሰፈሩ።
36፤ ከዔጽዮንጋብርም ተጕዘው በጺን ምድረ በዳ ሰፈሩ፤ ይህችም ቃዴስ ናት።
37፤ ከቃዴስም ተጕዘው በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ።
38፤ ካህኑም አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ሖር ተራራ ላይ ወጣ፥ በዚያም የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በአርባኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ።
39፤ አሮንም በሖር ተራራ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ሦስት ዓመት ነበር።
40፤ በከነዓን ምድርም በደቡብ በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ የእስራኤል ልጆች እንደ መጡ ሰማ።
41፤ እነርሱም ከሖር ተራራ ተጕዘው በሴልሞና ሰፈሩ።
42፤ ከሴልሞናም ተጕዘው በፉኖን ሰፈሩ።
43፤ ከፉኖንም ተጕዘው በኦቦት ሰፈሩ።
44፤ ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ዳርቻ ባለው በጋይ ሰፈሩ።
45፤ ከጋይም ተጕዘው በዲቦንጋድ ሰፈሩ።
46፤ ከዲቦንጋድም ተጕዘው በዓልሞንዲብላታይም ሰፈሩ።
47፤ ከዓልሞንዲብላታይምም ተጕዘው በናባው ፊት ባሉ በዓብሪም ተራሮች ላይ ሰፈሩ።
48፤ ከዓብሪምም ተራሮች ተጕዘው በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ባለው በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ።
49፤ በዮርዳኖስም አጠገብ በሞዓብ ሜዳ ላይ ከቤትየሺሞት እስከ አቤልሰጢም ድረስ ሰፈሩ።
50፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
51፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥
52፤ የአገሩን ሰዎች ሁሉ ከፊታችሁ ታሳድዳላችሁ፥ የተቀረጹትንም ድንጋዮቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ በኮረብታ ላይ ያሉትን መስገጃዎቻቸውንም ታፈርሳላችሁ፤
53፤ ምድሪቱንም ለእናንተ ርስት አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁና ምድሪቱን ትወርሱአታላችሁ ትቀመጡባታላችሁም።
54፤ ምድሪቱንም በየወገኖቻችሁ በዕጣ ትወርሳላችሁ፤ ለብዙዎች እንደ ብዛታቸው ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣላችሁ፤ እያዳንዱ ሁሉ ዕጣ እንደ ወደቀለት በዚያ ርስቱ ይሆናል፤ በየአባቶቻችሁ ነገዶች ትወርሳላችሁ።
55፤ የአገሩንም ሰዎች ከፊታችሁ ባታሳድዱ፥ ያስቀራችኋቸው ለዓይናችሁ እንደ እሾህ ለጎናችሁም እንደሚወጋ ነገር ይሆኑባችኋል፥ በምትቀመጡባትም ምድር ያስጨንቁአችኋል።
56፤ እኔም በእነርሱ አደርገው ዘንድ ያሰብሁትን በእናንተ አደርግባችኋለሁ።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]