መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

መጽሐፈ ሳሙኤል ካል - 2 Samuel

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24

1፤ ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ለዳዊት ልጅ ለአቤሴሎም አንዲት የተዋበች እኅት ነበረችው፥ ስምዋም ትዕማር ነበረ፤ የዳዊትም ልጅ አምኖን ወደዳት።
2፤ አምኖንም ከእኅቱ ከትዕማር የተነሣ እጅግ ስለ ተከዘ ታመመ፤ ድንግልም ነበረችና አንዳች ያደርጋት ዘንድ በዓይኑ ፊት ጭንቅ ሆኖበት ነበር።
3፤ ለአምኖንም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ የሚባል ወዳጅ ነበረው፤ ኢዮናዳብም እጅግ ብልህ ሰው ነበረ።
4፤ እርሱም። የንጉሥ ልጅ ሆይ፥ ስለ ምን ቀን በቀን እንዲህ ከሳህ? አትነግረኝምን? አለው። አምኖንም። የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን እወድዳታለሁ አለው።
5፤ ኢዮናዳብም። ታምሜአለሁ ብለህ በአልጋህ ላይ ተኛ፤ አባትህም ሊያይህ በመጣ ጊዜ። እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ የምበላውን እንጀራ እንድትሰጠኝ፥ መብሉንም እኔ እያየሁ እንድታዘጋጅልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላው እለምንሃለሁ በል አለው።
6፤ እንዲሁም አምኖን። ታምሜአለሁ ብሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊያየው በመጣ ጊዜ አምኖን ንጉሡን። እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ እያየሁ ሁለት እንጎቻ እንድታደርግልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላ እለምንሃለሁ አለው።
7፤ ዳዊትም። መብልን ታዘጋጂለት ዘንድ ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሂጂ ብሎ መልእክተኞችን ወደ ትዕማር ቤት ላከ።
8፤ ትዕማርም ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን ቤት ሄደች፥ ተኝቶም ነበር፤ ዱቄትም ወስዳ ለወሰች፥ እያየም እንጎቻ አደረገች፥ ጋገረችም።
9፤ ምጣዱንም ወስዳ በፊቱ ገለበጠች እርሱ ግን ይበላ ዘንድ እንቢ አለ። አምኖንም። ሰውን ሁሉ ከእኔ ዘንድ አስወጡ አለ፤ ሰውም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ወጣ።
10፤ አምኖንም ትዕማርን። ከእጅሽ እበላ ዘንድ መብሉን ወደ እልፍኙ አግቢው አላት፤ ትዕማርም የሠራችውን እንጎቻ ወስዳ ወንድምዋ አምኖን ወዳለበት እልፍኝ አገባችው።
11፤ መብሉንም ባቀረበች ጊዜ ያዛትና። እኅቴ ሆይ፥ ነዪ ከእኔም ጋር ተኚ አላት።
12፤ እርስዋ መልሳ። ወንድሜ ሆይ፥ አይሆንም፤ እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ዘንድ አይገባምና አታሳፍረኝ፤ ይህንም ነውረኛ ሥራ አታድርግ።
13፤ እኔም ነውሬን ወዴት ልሸከም? አንተም በእስራኤል ዘንድ ከምናምንቴዎች እንደ አንዱ ትሆናለህ፤ እንግዲህስ ለንጉሡ ንገረው፥ እኔንም አይነሣህም አለችው።
14፤ ቃልዋን ግን አልሰማም፤ ከእርስዋም ይልቅ ብርቱ ነበረና በግድ አስነወራት፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ።
15፤ ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፤ አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ። አምኖንም። ተነሥተሽ ሂጂ አላት።
16፤ እርስዋም። አይሆንም፤ ቀድሞ ከሠራኸው ክፋት ይልቅ አኔን በማውጣትህ የበለጠ ክፋት ትሠራለህ አለችው፤ እርሱ ግን አልሰማትም።
17፤ የሚያገለግለውንም ብላቴና ጠርቶ። ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት አለው።
18፤ ብዙ ኅብር ያለውንም ልብስ ለብሳ ነበር፥ እንዲህ ያለውን ልብስ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ ይለብሱ ነበርና፤ አገልጋዩም አስወጥቶ በሩን ዘጋባት።
19፤ ትዕማርም በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ፥ ብዙ ኅብርም ያለውን ልብስዋን ተርትራ፥ እጅዋንም በራስዋ ላይ ጭና እየጮኸች ሄደች።
20፤ ወንድምዋም አቤሴሎም። ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበረን? እኅቴ ሆይ፥ አሁን ግን ዝም በዪ፤ ወንድምሽ ነው፤ ይህን ነገር በልብሽ አትያዢው አላት። ትዕማርም በወንድምዋ በአቤሴሎም ቤት ብቻዋን ተቀመጠች።
21፤ ንጉሡም ዳዊት ይህን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ ነገር ግን የበኵር ልጁ ነበረና ስለ ወደደው የልጁን የአምኖን ነፍስ አላሳዘነም።
22፤ አቤሴሎምም እኅቱን ትዕማርን ስላሳፈራት አምኖንን ጠልቶታልና አቤሴሎም አምኖንን ክፉም ሆነ መልካምም አልተናገረውም።
23፤ ከሁለት ዓመትም በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር በጎቹን አሸለተ፤ አቤሴሎምም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ጠራ።
24፤ አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ መጥቶ። እነሆ፥ ባሪያህ በጎቹን ያሸልታል፤ ንጉሡና ሎሌዎቹ ከባሪያህ ጋር ይሂዱ አለው።
25፤ ንጉሡም አቤሴሎምን። ልጄ ሆይ፥ እንከብድብሃለንና ሁላችን እንመጣ ዘንድ አይሆንም አለው። የግድም አለው፥ እርሱ ግን መረቀው እንጂ ለመሄድ እንቢ አለ።
26፤ አቤሴሎምም። አንተ እንቢ ካልህ ወንድሜ አምኖን ከእኛ ጋር እንዲሄድ እለምንሃለሁ አለ። ንጉሡም። ከአንተ ጋር ለምን ይሄዳል? አለው።
27፤ አቤሴሎምም የግድ አለው፥ አምኖንንና የንጉሡንም ልጆች ሁሉ ከእርሱ ጋር ሰደደ።
28፤ አቤሴሎምም እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ አደረገ፤ አቤሴሎምም አገልጋዮቹን። አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ ልቡን ደስ ባለው ጊዜ እዩ። አምኖንን ግደሉ ባልኋችሁም ጊዜ ግደሉት፥ አትፍሩም፤ ያዘዝኋችሁም እኔ ነኝና በርቱ ጽኑም ብሎ አዘዛቸው።
29፤ የአቤሴሎም አገልጋዮች አቤሴሎም እንዳዘዛቸው በአምኖን ላይ አደረጉበት። የንጉሡም ልጆች ሁሉ ተነሥተው በየበቅሎቻቸው ተቀምጠው ሸሹ።
30፤ ገናም በመንገድ ሲሄዱ ለዳዊት። አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ገድሎአል፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም የሚል ወሬ መጣለት።
31፤ ንጉሡም ተነሥቶ ልብሱን ቀደደ፥ በምድር ላይም ወደቀ፤ ባሪያዎቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀድደው በአጠገቡ ቆሙ።
32፤ የዳዊትም ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ። ጌታዬ ጕልማሶቹ የንጉሡ ልጆች ሁሉ እንደ ሞቱ አያስብ፤ እኅቱን ትዕማርን በግድ ካስነወራት ጀምሮ በአቤሴሎም ዘንድ የተቈረጠ ነገር ነበረና የሞተ አምኖን ብቻ ነው።
33፤ አሁንም የሞተ አምኖን ብቻ ነው እንጂ የንጉሥ ልጆች ሁሉ ሞቱ ብሎ ጌታዬ ንጉሡ ይህን ነገር በልቡ አያኑር አለው።
34፤ አቤሴሎምም ኰበለለ። ጕበኛውም ጕልማሳ ዓይኑን ከፍ አደረገ፥ እነሆም፥ ብዙ ሰዎች በኋላው በተራራው አጠገብ በመንገድ ሲመጡ አየ።
35፤ ኢዮናዳብም ንጉሡን። እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤ ባሪያህ እንዳለው እንዲሁ ሆኖአል አለው።
36፤ ተናግሮም በጨረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ ወዲያው የንጉሥ ልጆች ገቡ፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ደግሞ ንጉሡና ባሪያዎቹ ሁሉ እጅግ ታላቅ ልቅሶ አለቀሱ።
37፤ አቤሴሎም ግን ኰብልሎ ወደ ጌሹር ንጉሥ ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ። ዳዊትም ሁልጊዜ ለልጁ ያለቅስ ነበር።
38፤ አቤሴሎም ኰብልሎ ወደ ጌሹር ሄደ፥ በዚያም ሦስት ዓመት ያህል ተቀመጠ።
39፤ ንጉሡም ዳዊት ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ ወደ አቤሴሎም ይሄድ ዘንድ እጅግ ናፈቀ።

የገጽ ጫፍ  | የሚቀጥለው ምዕራፍ  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]