መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
መጽሐፈ ሳሙኤል ካል - 2 Samuel
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
15
16
17
18
19
20
21
22
23
24
1
፤ በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል ቀጥሎ ራብ ሆነ፤ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ፊት ጠየቀ። እግዚአብሔርም። የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት አለ።
2
፤ ንጉሡም የገባዖንን ሰዎች ጠራ፤ የገባዖን ሰዎችም ከአሞራውያን የተረፉ ነበሩ እንጂ ከእስራኤል ልጆች ወገን አልነበሩም፤ የእስራኤልም ልጆች ምለውላቸው ነበር፤ ሳኦል ግን ለእስራኤል ልጆችና ለይሁዳ ስለ ቀና ሊገድላቸው ወድዶ ነበር።
3
፤ ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች። የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ምን ላድርግላችሁ? ማስተስረያውስ ምንድር ነው? አላቸው።
4
፤ የገባዖን ሰዎችም። በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ነገር አይደለም፤ ከእስራኤልም ወገን እኛ የምንገድለው የለም አሉት። እርሱም። የምትናገሩትን አደርግላችኋለሁ አለ።
5
፤ ንጉሡንም። እኛን ካጠፋ፥ በእስራኤልም ዳርቻ ሁሉ እንዳንቀመጥ መፍረሳችንን
6
፤ ካሰበው ሰው ልጆች ሰባት ሰዎች አሳልፈህ ስጠንና ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ ለእግዚአብሔር እንሰቅላቸዋለን አሉት። ንጉሡም። እሰጣችኋለሁ አለ።
7
፤ ንጉሡም በሳኦል ልጅ በዮናታንና በዳዊት መካከል ስለ ነበረው ስለ እግዚአብሔር መሐላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን አዳነ።
8
፤ ንጉሡም ለሳኦል የወለደቻቸውን የኢዮሄል ልጅ የሪጽፋን ሁለቱን ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን ለመሓላታዊውም ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደቻቸውን የሳኦልን ልጅ የሜሮብን አምስቱን ልጆች ወሰደ፥
9
፤ ለገባዖንም ሰዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፥ ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፤ እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ተገደሉ።
10
፤ የኢዮሄልም ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ ከመከር ወራት ጀምሮ ዝናብ ከሰማይ እስኪዘንብ ድረስ በድንጋይ ላይ ዘረጋችው፤ በቀንም ወፎች በሌሊትም አራዊት ያርፉባቸው ዘንድ አልተወችም።
11
፤ የሳኦልም ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ለዳዊት ነገሩት።
12
፤ ዳዊትም ሄደ፥ ሳኦልንም በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤትሳን አደባባይ ከሰረቁት ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፤
13
፤ ከዚያም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ይዞ መጣ፤ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት ሰበሰቡ።
14
፤ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት በብንያም አገር በጼላ በአባቱ በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡም ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ስለ አገሩ የተለመነውን ሰማ።
15
፤ በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤልም መካከል ደግሞ ሰልፍ ነበረ፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹ ወረዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፤ ዳዊትም ደከመ።
16
፤ ከራፋይም ወገን የነበረው ይሽቢብኖብ ዳዊትን ይገድል ዘንድ አሰበ፤ የጦሩም ሚዛን ክብደት ሦስት መቶ ሰቅል ናስ ነበረ፥ አዲስም የጦር መሣሪያ ታጥቆ ነበር።
17
፤ የጽሩያም ልጅ አቢሳ አዳነው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለው። ያንጊዜም የዳዊት ሰዎች። አንተ የእስራኤልን መብራት እንዳታጠፋ ከእንግዲህ ወዲህ ከእኛ ጋር ለሰልፍ አትወጣም ብለው ማሉለት።
18
፤ ከዚህም በኋላ እንደ ገና በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ሆነ፥ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሳፍን ገደለ።
19
፤ ደግሞም በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፤ የቤተ ልሔማዊውም የየዓሬኦርጊም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው ጎልያድን ገደለ።
20
፤ ደግሞም በጌት ላይ ሰልፍ ሆነ፤ በዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ሁላሁሉ ሀያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፤ እርሱ ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ።
21
፤ እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሣማ ልጅ ዮናታን ገደለው።
22
፤ እነዚያም አራቱ በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በባሪያዎቹም እጅ ወደቁ።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]