መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
መጽሐፈ ነህምያ። - Nehemiah
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
1
፤ ሰንባላጥም ቅጥሩን እንደ ሠራን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፥ ተበሳጨም፥ በአይሁድም አላገጠ።
2
፤ በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊትም ፊት። እነዚህ ደካሞች አይሁድ የሚሠሩት ምንድር ነው? ይተዉላቸዋልን? ይሠዋሉን? በአንድ ቀንስ ይጨርሳሉን? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን? ብሎ ተናገረ።
3
፤ አሞናዊውም ጦብያ በአጠገቡ ቆሞ። በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል አለ።
4
፤ አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤ በምርኮ አገር ለብዝበዛ አሳልፈህ ስጣቸው።
5
፤ በደላቸውንም አትክደን፥ ኃጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፤ በሠራተኞች ፊት አስቆጥተውሃልና።
6
፤ ቅጥሩንም ሠራን፤ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኵሌታው ድረስ ተጋጠመ፤ የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ።
7
፤ ሰንባላጥና ጦብያም ዓረባውያንም አሞናውያንም አሽዶዳውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ።
8
፤ መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያሸብሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተማማሉ።
9
፤ ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን።
10
፤ ይሁዳም። የተሸካሚዎች ኃይል ደከመ፥ ፍርስራሹም ብዙ ነው፤ ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም አሉ።
11
፤ ጠላቶቻችንም። ወደ መካከላቸው እስክንመጣና እስክንገድላቸው ድረስ ሥራቸውንም እስክናስተጓጕል ድረስ አያውቁምና አያዩም አሉ።
12
፤ በአጠገባቸውም የተቀመጡት አይሁድ መጥተው። ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል ብለው አሥር ጊዜ ነገሩን።
13
፤ ከቅጥሩም በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው።
14
፤ አይቼም ተነሣሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም የቀሩትንም ሕዝብ። አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፥ ስለ ወንድሞቻችሁም ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ አልኋቸው።
15
፤ ጠላቶቻችንም ይህ ነገር እንደ ደረሰልን፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ፤ እኛም ሁላችን ወደ ቅጥሩ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን።
16
፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ እኵሌቶቹ ብላቴኖቼ ሥራ ይሠሩ ነበር፥ እኵሌቶቹም ጋሻና ጦር ቀስትና ጥሩርም ይዘው ነበር፤ አለቆቹም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር።
17
፤ ቅጥሩንም የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፥ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር።
18
፤ አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ።
19
፤ ታላላቆቹንና ሹማምቱን የቀሩትንም ሕዝብ። ሥራው ታላቅና ሰፊ ነው፥ እኛም በቅጥሩ ላይ ተበታትነናል፥ አንዱም ከሁለተኛው ርቆአል፤
20
፤ የቀንደ መለከቱን ድምፅ ወደምትሰሙበት ስፍራ ወደዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል አልኋቸው።
21
፤ ሥራውንም ሠራን ከማለዳ ወገግታም ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኵሌቶቹ ጦር ይይዙ ነበር።
22
፤ ደግሞም በዚያ ጊዜ ሕዝቡን። ሁላችሁ ከብላቴኖቻችሁ ጋር በኢየሩሳሌም ውስጥ እደሩ፤ በሌሊትም ጠባቂዎች ሁኑልን፥ በቀንም ሥሩ አልኋቸው።
23
፤ እኔና ወንድሞቼም ብላቴኖቼም በኋላዬም የነበሩት ጠባቂዎች ልብሳችንን አናወልቅም ነበር።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]