መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ትንቢተ ኢሳይያስ - Isaiah
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
15
16
17
18
19
20
21
22
23
24
25
26
27
28
29
30
31
32
33
34
35
36
37
38
39
40
41
42
43
44
45
46
47
48
49
50
51
52
53
54
55
56
57
58
59
60
61
62
63
64
65
66
1
፤ በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ።
2
፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ፤ ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፥ እነርሱም አመጹብኝ።
3
፤ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም፥ ሕዝቤም አላስተዋለም።
4
፤ ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ ርኵሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል።
5
፤ ደግሞስ ዓመፃ እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሰፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል።
6
፤ ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም።
7
፤ ምድራችሁ ባድማ ናት፤ ከተሞቻችሁ በእሳት ተቃጠሉ፤ እርሻችሁንም በፊታችሁ ሌሎች ይበሉታል፤ ባዕድ እንዳፈረሳት ምድር ባድማ ሆነች።
8
፤ የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፥ በዱባ አትክልትም እንዳለ ጎጆ፥ እንደተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች።
9
፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር።
10
፤ እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ።
11
፤ የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም።
12
፤ በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው?
13
፤ ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፤ ዕጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፤ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፤ በደልንም የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም።
14
፤ መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ።
15
፤ እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል።
16
፤ ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፥
17
፤ መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ።
18
፤ ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።
19
፤ እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤
20
፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።
21
፤ ፍርድ ሞልቶባት የነበረው የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፥ አሁን ግን ገዳዮች አሉባት።
22
፤ ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፤ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ።
23
፤ አለቆችሽ አመጸኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፤ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፥ ዋጋም ለማግኘት ይሮጣሉ፤ ለድሀ አደጉ አይፈርዱም፥ የመበለቲቱም ሙግት ወደ እነርሱ አይደርስም።
24
፤ ስለዚህ የእስራኤል ኃያል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በጠላቶቼ ላይ ቍጣዬን እፈጽማለሁ፥ የሚቋቋሙኝንም እበቀላለሁ።
25
፤ እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፥ ዝገትሽንም በጣም አነጻለሁ፥ ቆርቆሮሽንም ሁሉ አወጣለሁ፤
26
፤ ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያው ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ የታመነችም ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።
27
፤ ጽዮን በፍርድ ከእርሷም የሚመለሱ በጽድቅ ይድናሉ።
28
፤ በደለኞችና ኃጢአተኞች ግን በአንድነት ይሰበራሉ፥ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ይጠፋሉ።
29
፤ በወደዳችኋት የአድባር ዛፍ ታፍራላችሁና፥ ስለ መረጣችኋትም አትክልት እፍረት ይይዛችኋልና፤
30
፤ ቅጠልዋ እንደ ረገፈ ዛፍ፥ ውሃም እንደሌለባት አትክልት ትሆናላችሁና።
31
፤ ኃይለኛውም እንደ ተልባ ጭረት፥ ሥራውም እንደ ጠለሸት ይሆናል፤ አብረውም ይቃጠላሉ እነርሱንም የሚያጠፋ የለም።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]