መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ትንቢተ ኢሳይያስ - Isaiah

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50 51 52 53 54 55 56 57 58 59 60 61 62 63 64 65 66

1፤ እንዲህም ሆነ፤ በንጉሡ በሕዝቅያስ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጥቶ ወሰዳቸው።
2፤ የአሦርም ንጉሥ ራፋስቂስን ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፥ እርሱም በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛይቱ ኵሬ መስኖ አጠገብ ቆመ።
3፤ የቤቱም አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እርሱ ወጡ።
4፤ ራፋስቂስም አላቸው። ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ይህ የምትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው?
5፤ እኔ። ለሰልፍ የሆነው ምክርህና ኃያልህ ከንቱ ነገር ነው አልሁ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው?
6፤ እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል ያቈስለውማል የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ አንዲሁ ነው።
7፤ አንተም። በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትለኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን። በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ይስፈረሰ ይህ አይደለምን?
8፤ አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ።
9፤ ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሶኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል?
10፤ አሁንም በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን አገር አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር። ወደዚህ አገር ወጥተህ አጥፋው አለኝ።
11፤ ኤልያቄምና ሳምናስ ዮአስም ራፋስቂስን። እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን አሉት።
12፤ ራፋስቂስ ግን። ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን? አላቸው።
13፤ ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ። የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ።
14፤ ንጉሡ እንዲህ ይላል። ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤
15፤ ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።
16፤ ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፥ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤
17፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለበት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው።
18፤ ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን?
19፤ የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን?
20፤ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?
21፤ እነርሱም ዝም አሉ፥ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ አንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና።
22፤ የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፥ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]