መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ትንቢተ ኤርምያስ - Jeremiah

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50 51 52

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በባቢሎን ላይና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ አጥፊውን ነፋስ አስነሣለሁ።
2 በባቢሎንም ላይ የሚያዘሩትን ሰዎች እሰድዳለሁ እነርሱም ያዘሩአታል፥ ምድርዋንም ባዶ ያደርጋሉ፤ በመከራም ቀን በዙሪያዋ ይከብቡአታል።
3 በወርዋሪው ላይ በጥሩርም በሚነሣው ላይ ቀስተኛው ቀስቱን ይገትር፤ ለጐበዛዝትዋ አትዘኑ ሠራዊትዋንም ሁሉ አጥፉ።
4 በከለዳውያንም ምድር ተገድለው፥ በሜዳዋም ላይ ተወግተው ይወድቃሉ።
5 ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል ምንም እንኳ የተሞላች ብትሆን፥ እስራኤልም ሆነ ይሁዳ በአምላኩ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ዘንድ አልተጣለም።
6 ከባቢሎን ውስጥ ሽሹ፥ እያንዳንዳችሁም ነፍሳችሁን አድኑ፤ በበደልዋ አትጥፉ፥ የእግዚአብሔር በቀል ጊዜ ነውና፥ እርሱም ብድራትዋን ይከፍላታልና።
7 ባቢሎን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ምድርን ሁሉ ያሰከረች የወርቅ ጽዋ ነበረች፥ አሕዛብም ከጠጅዋ ጠጥተዋል፤ ስለዚህ አሕዛብ አብደዋል።
8 ባቢሎን በድንገት ወድቃ ጠፍታለች፤ አልቅሱላት፥ ትፈወስም እንደ ሆነ ለKWsልዋ መድኃኒት ውሰዱላት።
9 ባቢሎንን ፈወስናት፥ እርስዋ ግን አልተፈወሰችም፤ ፍርድዋ እስከ ሰማይ ደርሶአልና፥ እስከ ደመናም ድረስ ከፍ ከፍ ብሎአልና ትታችኋት እያንዳንዳችን ወደ አገራችን እንሂድ።
10 እግዚአብሔር ጽድቃችንን አውጥቶአል፤ ኑ፥ በጽዮን የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ሥራ እንናገር።
11 ፍላጾችን ሳሉ ጋሻዎችንም አዘጋጁ፤ እግዚአብሔር ያጠፋት ዘንድ አሳቡ በባቢሎን ላይ ነውና የሜዶንን ነገሥታት መንፈስ አስነሥቶአል፤ የእግዚብሔር በቀል የመቅደሱ በቀል ነውና።
12 በባቢሎን ቅጥር ዓላማውን አንሡበት፥ ጥበቃን አጽኑ፥ ተመልካቾችን አቁሙ፥ ድብቅ ጦር አዘጋጁ። እግዚአብሔር በባቢሎን በሚኖሩት ላይ የተናገረውን አስቦአልና፥ አድርጎአልምና።
13 አንቺ በብዙ ውኃ አጠገብ የተቀመጥሽ፥ በመዝገብም የበለጠግሽ ሆይ፥ እንደ ስስትሽ መጠን ፍጻሜሽ ደርሶአል።
14 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል። በእውነት ሰዎችን እንደ አንበጣ እሞላብሻለሁ፥ እነርሱም ጩኸት ያነሡብሻል።
15 ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።
16 ድምጹን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናብም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፍስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል።
17 ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፎአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና።
18 እነርሱም ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ።
19 የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፥ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና፤ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
20 አንቺ መዶሻዬና የጦር መሣሪያዬ ነሽ፤ በአንቺ አሕዛብን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም መንግሥታትን አጠፋለሁ፤
21 በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እሰባብራለሁ፤
22 በአንቺም ሰረገላውንና በላዩ የሚቀመጠውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ወንድንና ሴትን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ሽማግሌውንና ብላቴናውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ጐልማሳውንና ቆንጆይቱን እሰባብራለሁ፤
23 በአንቺም እረኛውንና መንጋውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም አራሹንና ጥማጁን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም አለቆችንና ሹማምቶችን አሰባብራለሁ።
24 በጽዮን በዓይናችሁ ፊት ስለሠሩት ክፋታቸው ሁሉ በባቢሎንና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ፍዳቸውን እከፍላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
25 አንተ ምድርን ሁሉ የምታጠፋ አጥፊ ተራራ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እጄንም እዘረጋብሃለሁ፥ ከድንጋዮችም ላይ አንከባልልሃለሁ፥ የተቃጠለም ተራራ አደርግሃለሁ።
26 ከአንተም ለማዕዘንና ለመሠረት የሚሆን ድንጋይ አይወስዱም፥ ለዘላለምም ባድማ ትሆናለህ፥ ይላል እግዚአብሔር።
27 በምድር ላይ ዓላማን አንሡ በአሕዛብም መካከል መለከት ንፉ፥ አሕዛብንም አዘጋጁባት፤ የአራራትንና የሚኒን የአስከናዝንም መንግሥታት ሰብስቡባት አለቃንም በላይዋ አቁሙ፤ እንደ ጠgWraም ኩብኩባ ፈረሶችን በላይዋ አውጡ።
28 አሕዛብን የሚዶንንም ነገሥታት አለቆችንም ሹማምቶችንም ሁሉ የግዛታቸውንም ምድር ሁሉ አዘጋጁባት።
29 ማንም እንዳይቀመጥባት የባቢሎንን ምድር ባድማ ያደርጋት ዘንድ የእግዚአብሔር አሳብ በባቢሎን ላይ ጸንቶአልና ምድር ተናወጣለች ታመመችም።
30 የባቢሎን ኃያላን መዋጋትን ትተዋል በአምባዎቻቸውም ውስጥ ተቀምጠዋል፤ ኃይላቸውም ጠፍቶአል እንደ ሴቶችም ሆነዋል፤ ማደሪያዎችዋም ነድደዋል መወርወሪያዎችዋም ተሰብረዋል።
31-
32 ከዳር እስከ ዳር ድረስ ከተማው እንደ ተያዘች መልካምዎችዋም እንደ ተያዙ፥ ቅጥርዋም በእሳት እንደ ተቃጠለ፥ ሰልፈኞችም እንደ ደነገጡ ለባቢሎን ንጉሥ ይነግር ዘንድ ወሬኛው ወሬኛውን መልእክተኛውም መልእክተኛውን ሊገናኝ ይሮጣል።
33 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። አውድማ እንደ ተረገጠ ጊዜ፥ እንዲሁ የባቢሎን ልጅ ናት፤ ጥቂት ቈይታ የመከር ጊዜ ይደርስባታል።
34 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላኝ፥ ከፋፈለኝም፥ እንደ ባዶ ዕቃም አደረገኝ፥ እንደ ዘንዶም ዋጠኝ፥ ከሚጣፍጠውም ምግቤ ሆዱን ሞላ፥ እኔንም ጣለኝ።
35 በጽዮን የምትቀመጥ። በእኔና በሥጋዬ የተደረገ ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን ትላለች፤ ኢየሩሳሌምም። ደሜ በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን ትላለች።
36 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እምዋገትልሻለሁ በቀልሽንም እበቀልልሻለሁ፤ ባሕርዋንም ድርቅ አደርገዋለሁ ምንጭዋንም አደርቀዋለሁ።
37 ባቢሎንም የድንጋይ KWlልና የቀበሮ ማደሪያ መደነቂያም ማፍዋጫም ትሆናለች፥ የሚቀመጥባትም ሰው አይገኝም።
38 በአንድነትም እንደ አንበሶች ያገሣሉ፥ እንደ አንበሳም ደቦሎች ያጕረመርማሉ።
39 በሞቃቸው ጊዜ ደስ እንዲላቸው ለዘላለምም አንቀላፍተው እንዳይነቁ የመጠጥ ግብዣ አደርግላቸዋለሁ አሰክራቸውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
40 እንደ ጠቦቶችና እንደ አውራ በጎች እንደ አውራ ፍየሎችም ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ።
41 ሼሻክ እንዴት ተያዘች! የምድርም ሁሉ ምስጋና እንዴት ተወሰደች! ባቢሎንም በአሕዛብ መካከል መደነቂያ እንዴት ሆነች!
42 ባሕር በባቢሎን ላይ ወጣ በሞገዱም ብዛት ተከደነች።
43 ከተሞችዋ ባድማና ደረቅ ምድር ምድረ በዳም፥ ሰውም የማይቀመጥበት የሰውም ልጅ የማያልፍበት ምድር ሆኑ።
44 በባቢሎንም ውስጥ ቤልን እቀጣለሁ የዋጠውንም ከአፉ አስተፋዋለሁ፤ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርሱ አይሰበሰቡም፥ የባቢሎንም ቅጥር ይወድቃል።
45 ሕዝቤ ሆይ፥ ከመካከልዋ ውጡ እያንዳንዳችሁም ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ራሳችሁን አድኑ።
46 በምድርም ከሚሰማ ወሬ የተነሣ አትፍሩ ልባችሁም የዛለ አይሁን፤ በአንድ ዓመት ወሬ ይመጣል፥ ከዚያም በኋላ በሌላው ዓመት ወሬ፥ በምድርም ላይ ግፍ ይመጣል፥ አለቃም በአለቃ ላይ ይነሣል።
47 ስለዚህ፥ እነሆ፥ የተቀረጹትን የባቢሎን ምስሎች የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፥ ምድርዋም ሁሉ ታፍራለች፤ ተወግተውም የሞቱት ሁሉ በመካከልዋ ይወድቃሉ።
48 አጥፊዎች ከሰሜን ይመጡባታልና ሰማይና ምድር በእነርሱም ያለው ሁሉ ስለ ባቢሎን እልል ይላሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
49 ባቢሎንም ከእስራኤል ተወግተው የሞቱት እንዲወድቁ እንዳደረገች፥ እንዲሁ በባቢሎን ከምድሩ ሁሉ ተወግተው የሞቱት ይወድቃሉ።
50 ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ፥ ሂዱ፥ አትቁሙ፤ እግዚአብሔርን ከሩቅ አስቡ፥ ኢየሩሳሌምንም በልባችሁ አስቡ።
51 ስድብን ስለ ሰማን አፍረናል፤ ባዕዳን ሰዎችም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገብተዋልና ነውር ፊታችንን ከድኖታል።
52 ስለዚህ፥ እነሆ፥ የተቀረጹትን ምስሎችዋ የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር በምድርዋም ላይ ሁሉ የተወጉት ያንቋርራሉ።
53 ባቢሎን ምንም ወደ ሰማይ ብትወጣ፥ የኃይልዋንም ከፍታ ብታጸና፥ ከእኔ ዘንድ አጥፊዎች ይመጡባታል፥ ይላል እግዚአብሔር።
54 ከባቢሎን ጩኸት፥ ከከለዳውያንም ምድር የታላቅ ጥፋት ድምፅ ተሰምቶአል።
55 እግዚአብሔር ባቢሎንን አጥፍቶአታልና፥ ከእርስዋም ታላቁን ድምፅ ዝም አሰኝቶአልና፤ ሞገዳቸውም እንደ ብዙ ውኆች ይተምማል፥ የድምፃቸውም ጩኸት ተሰምቶአል።
56 አጥፊው በባቢሎን ላይ መጥቶባታልና፥ ኃያላኖችዋ ተያዙ፥ ቀስታቸውም ተሰባበረ፤ እግዚአብሔር ፍዳን የሚከፍል አምላክ ነውና፥ ፍዳንም በእርግጥ ይከፍላል።
57 መሳፍንቶችዋንና ጥበበኞችዋንም፥ አለቆችዋንና ሹማምቶችዋን ኃያላኖችዋንም አሰክራለሁ፥ ለዘላለምም አንቀላፍተው አይነቁም፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ።
58 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰፊው የባቢሎን ቅጥር ፈጽሞ ይፈርሳል ረጃጅሞችም በሮችዋ በእሳት ይቃጠላሉ፤ የወገኖችም ድካም ከንቱ ትሆናለች፥ የአሕዛብም ሥራ ለእሳት ትሆናለች፤ እነርሱም ይደክማሉ።
59 የመሕሤያ ልጅ የኔርያ ልጅ ሠራያ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ከእርሱ ጋር ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘው ቃል ይህ ነው። ሠራያም የቤት አዛዥ ነበረ።
60 በባቢሎንም ላይ የሚመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ፥ ስለ ባቢሎን የተጻፈውን ይህን ቃል ሁሉ፥ ኤርምያስ በመጽሐፍ ላይ ጻፈው።
61 ኤርምያስም ሠራያን እንዲህ አለው። ወደ ባቢሎን በገባህ ጊዜ እይ ይህንም ቃል ሁሉ አንብብና።
62 አቤቱ፥ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ማንም እንዳይቀመጥባት፥ ለዘላለምም ባድማ እንድትሆን ታጠፋት ዘንድ በዚህች ስፍራ ላይ ተናግረሃል በል።
63 ይህንም መጽሐፍ ማንበብ ከፈጸምህ በኋላ፥ ድንጋይን እሰርበት በኤፍራጥስም ውስጥ ጣለው፤
64 አንተም። እኔ ከማመጣባት ክፉ ነገር የተነሣ እንዲሁ ባቢሎን ትሰጥማለች አትነሣምም በል። የኤርምያስ ቃል እስከዚህ ድረስ ነው።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]