መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ትንቢተ ዘካርያስ - Zechariah

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14

1፤ ዓይኖቼንም አነሣሁ፤ እነሆም፥ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ አንድ ሰውን አየሁ።
2፤ እኔም። አንተ ወዴት ትሄዳለህ? አልሁ። እርሱም። የኢየሩሳሌምን ወርድና ርዝመት ስንት መሆኑን ሰፍሬ አይ ዘንድ እሄዳለሁ አለኝ።
3፤ እነሆም፥ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጣ፥ ሌላም መልአክ ሊገናኘው ወጣ፥
4፤ እንዲህም አለው። ሩጥ፥ ይህንም ጕልማሳ እንዲህ በለው። ኢየሩሳሌም በውስጥዋ ካሉት ሰዎችና እንስሶች ብዛት የተነሣ ቅጥር እንደሌላቸው መንደሮች ሆና ትኖራለች።
5፤ እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፥ በውስጥዋም ክብርን እሆናለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
6፤ እናንተ ሆይ፥ ከሰሜን ምድር ሽሹ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እንደ አራቱ የሰማይ ነፍሳት በትኛችኋለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
7፤ አንቺ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ጽዮን ሆይ፥ ኰብልዪ።
8፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ከክብሩ በኋላ ወደ በዘበዙአችሁ አሕዛብ ልኮኛል፤ የሚነካችሁ የዓይኑን ብሌን የሚነካ ነውና።
9፤ እነሆ፥ እጄን በላያቸው አወዛውዛለሁ፥ ተገዝተው ለነበሩት ብዝበዛ ይሆናሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።
10፤ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ መጥቼ በመካከልሽ እኖራለሁና ዘምሪ ደስም ይበልሽ፥ ይላል እግዚአብሔር።
11፤ በዚያም ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፥ ሕዝብም ይሆኑኛል፤ በመካከልሽም እኖራለሁ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂአለሽ።
12፤ እግዚአብሔርም ይሁዳን እድል ፈንታው አድርጎ በተቀደሰችው ምድር ይወርሰዋል፥ ኢየሩሳሌምንም ዳግመኛ ይመርጣል።
13፤ እግዚአብሔር ከተቀደሰ ማደሪያው ነቅቶአልና ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሆይ፥ በፊቱ ዝም በል።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  |  መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]