መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ትንቢተ ዘካርያስ - Zechariah
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
1
፤ በንጉሡም በዳርዮስ በአራተኛው ዓመት ካሴሉ በሚባል በዘጠነኛው ወር በአራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ መጣ።
2
፤ የቤቴልም ሰዎች ሳራሳርንና ሬጌሜሌክን ሰዎቻቸውንም በእግዚአብሔር ፊት ይለምኑ ዘንድ፥
3
፤ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ቤት ካህናት ለነቢያትም። ባለፉት ዓመታት እንዳደረግሁት በአምስተኛው ወር መለየትና ማልቀስ ይገባኛልን? ብለው ይናገሩ ዘንድ ልኮአቸው ነበር።
4
፤ የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
5
፤ ለምድሩ ሕዝብ ሁሉ ለካህናትም እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። በዚህ በሰባው ዓመት በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር በጾማችሁና ባለቀሳችሁ ጊዜ፥ በውኑ ለእኔ ጾም ጾማችሁልኝ?
6
፤ በምትበሉበትና በምትጠጡበትስ ጊዜ፥ ለራሳችሁ የምትበሉና የምትጠጡ አይደላችሁምን?
7
፤ ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ገና ሰዎች ባሉባቸው ጊዜ፥ በምቾትም ተቀምጠው ሳሉ፥ ደቡቡና ቈላውም ሰዎች ባሉባቸው ጊዜ፥ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት እጅ የተናገረውን ቃል መስማት አይገባችሁምን?
8
፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ።
9
፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮአል። እውነተኛውን ፍርድ ፍረዱ፤ ቸርነትንና ምሕረትን ሁላችሁ ለወንድሞቻችሁ አድርጉ፤
10
፤ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን፥ መጻተኛውንና ችግረኛውን አትበድሉ፤ ከእናንተም ማንም በወንድሙ ላይ ክፉውን ነገር በልቡ አያስብ።
11
፤ እነርሱ ግን ደንደሳቸውን አዞሩ እንጂ መስማትን እምቢ አሉ፤ እንዳይሰሙም ጆሮአቸውን አደነቈሩ።
12
፤ የሠራዊትም ጌታ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት እጅ በመንፈሱ የላከውን ሕጉንና ቃሉን እንዳይሰሙ ልባቸውን እንደ አልማዝ አጠነከሩ፤ ስለዚህ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ቍጣ መጣ።
13
፤ እኔ በጠራሁ ጊዜ እነርሱ እንዳልሰሙኝ፥ እንዲሁ እነርሱ በሚጠሩበት ጊዜ እኔ አልሰማም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤
14
፤ ወደማያውቁአቸውም አሕዛብ ሁሉ በዐውሎ ነፋስ በተንኋቸው። እንዲሁ ከእነርሱ በኋላ ምድሪቱ ባድማ ሆናለች፥ የሚተላለፍባትና የሚመላለስባትም አልነበረም፤ ያማረችውንም ምድር ባድማ አደረጉአት።
የገጽ ጫፍ
|
የሚቀጥለው ምዕራፍ
|
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]