መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ። - 1 Kings
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
15
16
17
18
19
20
21
22
1
፤ ንጉሡ ዳዊትም ሸመገለ ዕድሜውም በዛ፤ ልብስም ደረቡለት፥ ነገር ግን አይሞቀውም ነበር።
2
፤ ባሪያዎቹም። ለጌታችን ለንጉሡ ድንግል ትፈለጋለች፤ በንጉሡም ፊት ቆማ ታገልግለው፥ በጌታችንም በንጉሡ ብብት ተኝታ ታሙቀው አሉት።
3
፤ በእስራኤልም አገር ሁሉ የተዋበች ቈንጆ ፈለጉ፤ ሱነማይቱን አቢሳንም አገኙ፥ ወደ ንጉሡም ይዘዋት መጡ።
4
፤ ቈንጆይቱም እጅግ ውብ ነበረች፤ ንጉሡንም ትረዳውና ታገለግለው ነበር፥ ንጉሡ ግን አያውቃትም ነበር።
5
፤ የአጊትም ልጅ አዶንያስ። ንጉሥ እሆናለሁ ብሎ ተነሣ፤ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ።
6
፤ አባቱም ከቶ በሕይወቱ ሳለ። እንዲህ ለምን ታደርጋለህ? ብሎ አልተቈጣውም ነበር፤ እርሱ ደግሞ እጅግ ያማረ ሰው ነበረ፤ ከአቤሴሎምም በኋላ ተወልዶ ነበር።
7
፤ ሴራውም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ነበረ፥ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ይረዱት ነበር።
8
፤ ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅና የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነቢዩም ናታን ሳሚም ሬሲም የዳዊትም ኃያላን ከአዶንያስ ጋር አልነበሩም።
9
፤ አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን ፍሪዳዎችንም በዓይንሮጌል አጠገብ ባለችው በዞሔሌት ድንጋይ ዘንድ ሠዋ፤ የንጉሡንም ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፥ የንጉሡንም ባሪያዎች፥ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ።
10
፤ ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያስንም፥ ኃያላኑንም፥ ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም።
11
፤ ናታንም የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ ብሎ ተናገራት። ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ እንደ ነገሠ አልሰማሽምን?
12
፤ አሁንም ነዪ፥ የልጅሽን የሰሎሞንን ነፍስና የአንቺን ነፍስ እንድታድኝ እመክርሻለሁ።
13
፤ ሄደሽ ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ግቢና። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ለእኔ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ አልማልህልኝምን? ስለ ምንስ አዶንያስ ይነግሣል? በዪው።
14
፤ እነሆ፥ አንቺ በዚያ ለንጉሥ ስትነግሪ እኔ ከአንቺ በኋላ እገባለሁ፥ ቃልሽንም አጸናለሁ።
15
፤ ቤርሳቤህም ወደ ንጉሡ ወደ እልፍኝ ገባች፤ ንጉሡም እጅግ ሸምግሎ ነበር፥ ሱነማይቱም አቢሳ ታገለግለው ነበር።
16
፤ ቤርሳቤህም አጐንብሳ ለንጉሡ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም። ምን ትፈልጊያለሽ? አለ።
17
፤ እርስዋም አለችው። ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ምለህልኛል፤
18
፤ አሁንም፥ እነሆ፥ አዶንያስ መንገሡ ነው፤ አንተም ጌታዬ ንጉሥ ይህን አታውቅም፤
19
፤ እርሱም ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ ካህኑንም አብያታርን፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን ጠርቶአል፤ ባሪያህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም።
20
፤ አሁንም፥ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሥ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ትነግራቸው ዘንድ የእስራኤል ሁሉ ዓይን ይመለከትሃል።
21
፤ ይህ ባይሆን፥ ጌታዬ ከአባቶችህ ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ኃጢአተኞች እንቈጠራለን።
22
፤ እነሆም፥ ለንጉሡ ስትናገር ነቢዩ ናታን ገባ።
23
፤ ለንጉሡም። እነሆ፥ ነቢዩ ናታን መጥቶአል ብለው ነገሩት፤ እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በገባ ጊዜ በግምባሩ በምድር ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ እጅ ነሣ።
24
፤ ናታንም አለ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ። ከእኔ በኋላ አዶንያስ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለሃልን?
25
፤ እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ የሠራዊትንም አለቃ ኢዮአብን፥ ካህኑንም አብያታርን ጠርቶአል፤ እነሆም፥ በፊቱ እየበሉና እየጠጡ። አዶንያስ ሺህ ዓመት ይንገሥ ይላሉ።
26
፤ ነገር ግን እኔን ባሪያህን፥ ካህኑንም ሳዶቅን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ ባሪያህንም ሰሎሞንን አልጠራም።
27
፤ በውኑ ይህ ነገር ከጌታዬ ከንጉሡ የተደረገ ነውን? ለባሪያህም ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አልነገርህምን?
28
፤ ንጉሡም ዳዊት። ቤርሳቤህን ጥሩልኝ ብሎ መለሰ። ወደ ንጉሡም ገባች፥ በንጉሡም ፊት ቆመች።
29
፤ ንጉሡም። ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን!
30
፤ በእውነት። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በእኔም ፋንታ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር እንደ ማልሁልሽ፥ እንዲሁ ዛሬ በእውነት አደርጋለሁ ብሎ ማለ።
31
፤ ቤርሳቤህም በግምባርዋ በምድር ላይ ተደፍታ ለንጉሡ እጅ ነሣችና። ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም በሕይወት ይኑር አለች።
32
፤ ንጉሡም ዳዊት። ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ጥሩልኝ አለ። ወደ ንጉሡም ፊት ገቡ።
33
፤ ንጉሡም አላቸው። የጌታችሁን ባሪያዎች ይዛችሁ ሂዱ፥ ልጄንም ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጡት፥ ወደ ግዮንም አውርዱት፤
34
፤ በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቅቡት፤ ቀንደ መለከትም ነፍታችሁ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ በሉ።
35
፤ በኋላውም ተከትላችሁ ውጡ፤ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፥ በእኔም ፋንታ ይንገሥ፤ በእስራኤልና በይሁዳም ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዣለሁ።
36
፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ መልሶ ለንጉሡ አለ፥ ያበጅ ያድርግ፤ የጌታዬም የንጉሥ አምላክ ይህን ይናገር።
37
፤ እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሥ ጋር እንደ ነበረ እንዲሁ ከሰሎሞን ጋር ይሁን፥ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሡ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርግ።
38
፤ ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፥ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት።
39
፤ ካህኑም ሳዶቅ ከድንኳኑ የቅብዓቱን ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባ፤ ቀንደ መለከትም ነፉ፤ ሕዝቡም ሁሉ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ አሉ።
40
፤ ሕዝቡም ሁሉ እርሱን ተከትለው ወጡ፥ ሕዝቡም ዘፈን ይዘፍኑ ነበር፥ በታላቅም ደስታ ደስ አላቸው፤ ከጩኸታቸውም የተነሣ ምድር ተናወጠች።
41
፤ አዶንያስና እርሱም የጠራቸው ሁሉ መብሉና መጠጡ ተፈጽሞ ሳለ ሰሙ፤ ኢዮአብም የቀንደ መለከት ጽምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ በከተማ ውስጥ ያለ የሽብር ድምፅ ምንድር ነው? አለ።
42
፤ እርሱም ይህን ሲናገር የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ፤ አዶንያስም። አንተ መልካም ሰው ነህና፥ መልካም ታወራልናለህና ግባ አለ።
43
፤ ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ብሎ መለሰ። በእውነት ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው።
44
፤ ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካሁኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ከሊታውያንንና ፈሊታውያንንም ሰደደ፥ በንጉሡም በቅሎ ላይ አስቀመጡት።
45
፤ ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት፤ ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጡ፥ ከተማይቱም አስተጋባች፤ የሰማችሁትም ድምፅ ይህ ነው።
46
፤ ደግሞም ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል።
47
፤ የንጉሡም ባሪያዎች ገብተው። እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ዙፋኑንም ከዙፋንህ የበለጠ ያድርግ ብለው ጌታችንን ንጉሡን ዳዊትን ባረኩ፤ ንጉሡም በአልጋው ላይ ሆኖ ሰገደ።
48
፤ ንጉሡም ደግሞ። ዓይኔ እያየ ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን አለ።
49
፤ አዶንያስም የጠራቸው ሁሉ ፈሩ፥ ተነሥተውም እያንዳንዳቸው በየመንገዳቸው ሄዱ።
50
፤ አዶንያስም ሰሎሞንን ፈራ፥ ተነሥቶም ሄደ፥ የመሠዊያውንም ቀንድ ያዘ።
51
፤ ለሰሎሞንም። እነሆ፥ አዶንያስ ንጉሡን ሰሎሞንን ፈርቶ። ንጉሡ ሰሎሞን ባሪያውን በሰይፍ እንዳይገድለኝ ዛሬ ይማልልኝ ብሎ የመሠዊያውን ቀንድ ይዞአል አሉት።
52
፤ ሰሎሞንም። እርሱ አካሄዱን ያሳመረ እንደ ሆነ ከእርሱ አንዲት ጠጕር እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም፤ ነገር ግን ክፋት የተገኘበት እንደ ሆነ ይሞታል አለ።
53
፤ ንጉሡ ሰሎሞንም ላከ፥ ከመሠዊያውም አወረዱት፤ መጥቶም ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ነሣ፥ ሰሎሞንም። ወደ ቤትህ ሂድ አለው።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]