መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ። - 1 Kings

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22

1፤ እነሆም፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፤ ኢዮርብዓምም ዕጣን እያጠነ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ነበር።
2፤ በመሠዊያውም ላይ። መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፥ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ።
3፤ በዚያም ቀን። እግዚአብሔር የተናገረው ምልክት ይህ ነው፤ እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፥ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል ብሎ ምልክት ሰጠ።
4፤ ንጉሡም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የጮኸውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ኢዮርብዓም እጁን ከመሠዊያው አንሥቶ። ያዙት አለ። በእርሱም ላይ የዘረጋት እጅ ደረቀች፥ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም።
5፤ የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፥ አመዱም ከመሠዊያው ፈሰሰ።
6፤ ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው። አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፥ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፥ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እንደ ቀድሞም ሆነች።
7፤ ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው። ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና እንጀራም ብላ፥ በረከትም እሰጥሃለሁ አለው።
8፤ የእግዚአብሔርም ሰው ንጉሡን። የቤትህን እኩሌታ እንኳ ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፥ በዚህም ስፍራ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፤
9፤ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ታዝዤአለሁና አለው።
10፤ በሌላም መንገድ ሄደ፥ ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ አልተመለሰም።
11፤ በቤቴልም አንድ ሽማግሌ ነቢይ ይቀመጥ ነበር፤ ልጆቹም ወደ እርሱ መጥተው በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ያደረገውን ሥራ ሁሉ ነገሩት ደግሞም ለንጉሡ የተናገረውን ቃል ሁሉ ለአባታቸው ነገሩት።
12፤ አባታቸውም። በማናቸው መንገድ ሄደ? አላቸው። ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ አመለከቱት።
13፤ ልጆቹንም። አህያውን ጫኑልኝ አላቸው፤ አህያውንም በጫኑለት ጊዜ ተቀመጠበት።
14፤ ከእግዚአብሔርም ሰው በኋላ ሄደ፤ በአድባርም ዛፍ በታች ተቀምጦ አገኘውና። ከይሁዳ የመጣህ የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
15፤ እርሱም። ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፥ እንጀራም ብላ አለው።
16፤ እርሱም። ከአንተ ጋር እመለስና እገባ ዘንድ አይቻለኝም፤ በዚህም ስፍራ ከአንተ ጋር እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፤
17፤ በዚያ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ተብሎልኛልና አለ።
18፤ እርሱም። እኔ ደግሞ እንደ አንተ ነቢይ ነኝ፤ መልአክም። እንጀራ ይበላ ዘንድ ውኃም ይጠጣ ዘንድ ከአንተ ጋር ወደ ቤትህ መልሰው ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተናገረኝ አለው። ዋሽቶም ተናገረው።
19፤ ከእርሱም ጋር ተመለሰ፥ በቤቱም እንጀራ በላ፥ ውኃም ጠጣ።
20፤ በማዕድም ተቀምጠው ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ መለሰው ነቢይ መጣ፤
21፤ ከይሁዳም ወደ መጣው ወደ እግዚአብሔር ሰው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእግዚአብሔር አፍ ላይ ዐምፀሃልና፥ አምላክህም እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህምና፥
22፤ ተመልሰህም። እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ ባለህ ስፍራ እንጀራ በልተሃልና፥ ውኃም ጠጥተሃልና ሬሳህ ወደ አባቶችህ መቃብር አይደርስም ብሎ ጮኸ።
23፤ እንጀራም ከበላ፥ ውኃም ከጠጣ በኋላ አህያውን ጫነለት።
24፤ ተመልሶም በሄደ ጊዜ በመንገዱ ላይ አንበሳ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋድሞ ነበር፥ አህያውም በእርሱ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ አንበሳውም ደግሞ በሬሳው አጠገብ ቆሞ ነበር።
25፤ እነሆም፥ መንገድ አላፊ ሰዎች ሬሳው በመንገዱ ወድቆ አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆሞ አዩ መጥተውም ሽማግሌው ነቢይ ተቀምጦባት በነበረው ከተማ አወሩ።
26፤ ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ያን በሰማ ጊዜ። በእግዚአብሔር አፍ ላይ ያመፀ ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል፥ እግዚአብሔር ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ሰብሮም ገድሎታል አለ።
27፤ ልጆቹንም። አህያ ጫኑልኝ አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት።
28፤ ሄደም፥ ሬሳውም በመንገድ ወድቆ፥ በሬሳውም አጠገብ አህያውና አንበሳው ቆመው፥ አንበሳው ሬሳውን ሳይበላው፥ አህያውንም ሳይሰብረው አገኘ።
29፤ ነቢዩም የእግዚአብሔርን ሰው ሬሳ አነሣ፥ በአህያውም ላይ ጭኖ መለሰው፤ ያለቅስለትና ይቀብረው ዘንድ ወደ ገዛ ከተማው ይዞት መጣ።
30፤ ሬሳውንም በገዛ መቃብሩ አኖረው፤ ዋይ ዋይ ወንድሜ ሆይ እያሉ አለቀሱለት።
31፤ ከቀበረውም በኋላ ልጆቹን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤
32፤ በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ፥ በሰማርያም ከተሞች ውስጥ ባሉ በኮረብታዎቹ መስገጃዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል የጮኸው ነገር በእውነት ይደርሳልና።
33፤ ከዚህም በኋላ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገድ አልተመለሰም፥ ነገር ግን ለኮረብታዎቹ መስገጃዎች አብልጦ ከሕዝብ ሁሉ ካህናትን አደረገ፤ የሚወድደውንም ሁሉ ይቀድስ ነበር፥ እርሱም ለኮርብታዎቹ መስገጃዎች ካህን ይሆን ነበር።
34፤ እስኪፈርስም ከምድርም እስኪጠፋ ድረስ ይህ ነገር ለኢዮርብዓም ቤት ኃጢአት ሆነ።

የገጽ ጫፍ  | የሚቀጥለው ምዕራፍ  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]