መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ። - 1 Kings

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22

1፤ ሰሎሞንም ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን አማች ሆነ፤ የፈርዖንን ልጅ አገባ፥ ቤቱንና የእግዚአብሔርንም ቤት በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ያለውን ቅጥር ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ ወደ ዳዊት ከተማ አመጣት።
2፤ እስከዚያም ቀን ድረስ ለእግዚአብሔር ስም መቅደስ አልተሠራም ነበርና ሕዝቡ በኮረብታ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋ ነበር።
3፤ ሰሎሞንም እግዚአብሔርን ይወድድ ነበር፥ በአባቱም በዳዊት ሥርዓት ይሄድ ነበር፤ ብቻ በኮረብታ መስገጃ ይሠዋና ያጥን ነበር።
4፤ ገባዖን ዋና የኮረብታ መስገጃ ነበረችና ንጉሡ ይሠዋ ዘንድ ወደዚያ ሄደ፤ ሰሎሞንም በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።
5፤ እግዚአብሔርም በገባዖን ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም። ምን እንድሰጥህ ለምን አለ።
6፤ ሰሎሞንም አለ። እርሱ በፊትህ በእውነትና በጽድቅ በልብም ቅንነት ከአንተ ጋር እንደ ሄደ፥ ከባሪያህ ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ቸርነት አድርገሃል፤ ዛሬ እንደ ሆነም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተህ ታላቁን ቸርነትህን አቆይተህለታል።
7፤ አሁንም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫንና መግቢያን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ።
8፤ ባሪያህም ያለው አንተ በመረጥኸው ሕዝብህ ስለ ብዛቱም ይቈጠርና ይመጠን ዘንድ በማይቻል በታላቅ ሕዝብ መካከል ነው።
9፤ ስለዚህም በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፥ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው፤ አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ይፈድ ዘንድ ማን ይችላል?
10፤ ሰሎሞንም ይህን ነገር ስለ ለመነ፥ ነገሩ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።
11፤ እግዚአብሔርም አለው። ፍርድን ትለይ ዘንድ ለራስህ ማስተዋልን ለመንህ እንጂ ለራስህ ብዙ ዘመናትን ባለጠግነትንም የጠላቶችህንም ነፍስ ሳትለምን ይህን ነገር ለምነሃልና እነሆ፥
12፤ እኔ እንደ ቃል አድርጌልሃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ።
13፤ ደግሞም ከነገሥታት የሚመስልህ ማንም እንዳይኖር ያልለመንኸውን ባለጠግነትና ክብር ሰጥቼሃለሁ።
14፤ አባትህም ዳዊት እንደ ሄደ፥ ሥርዓቴንና ትእዛዜን ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴ የሄድህ እንደ ሆነ፥ ዕድሜህን አረዝመዋለሁ።
15፤ ሰሎሞንም ነቃ፥ እነሆም፥ ሕልም ነበረ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጥቶ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት አቀረበ፥ ለባሪያዎቹም ሁሉ ግብዣ አደረገ።
16፤ በዚያን ጊዜም ሁለት ጋለሞቶች ሴቶች ወደ ንጉሡ መጥተው በፊቱ ቆሙ።
17፤ አንደኛይቱም ሴት አለች። ጌታዬ ሆይ፥ እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን፤ እኔም ከእርስዋ ጋር በቤት ሳለሁ ወለድሁ።
18፤ እኔ ከወለድሁ ከሦስት ቀን በኋላ ይህች ሴት ደግሞ ወለደች፤ እኛ በቤት ውስጥ አብረን ነበርን፥ ከሁለታችንም በቀር ማንም በቤት ውስጥ አልነበረም።
19፤ እርስዋም በላዩ ስለ ተኛችበት የዚህች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ።
20፤ እርስዋም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፥ እኔ ባሪያህ ተኝቼ ሳለሁ፥ ልጄን ከአጠገቤ ወሰደች፥ በብብትዋም አደረገችው፥ የሞተውንም ልጅዋን በእኔ ብብት አደረገች።
21፤ ልጄንም አጠባ ዘንድ በማለዳ ብነሣ፥ እነሆ፥ ሞቶ ነበር፤ ነገር ግን ብርሃን በሆነ ጊዜ ተመለከትሁት፥ እነሆም፥ የወለድሁት ልጄ አልነበረም።
22፤ ሁለተኛይቱም ሴት። ደኅነኛው የኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው እንጂ አንቺ እንደምትዪው አይደለም አለች። ይህችም። የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፥ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው አለች፤ እንዲሁም በንጉሡ ፊት ይነጋገሩ ነበር።
23፤ በዚያን ጊዜም ንጉሡ። ይህች። ደኅነኛው የእኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው ትላለች፤ ያችኛይቱም። አይደለም፥ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው ትላለች አለ።
24፤ ንጉሡም። ሰይፍ አምጡልኝ አለ፤ ሰይፍም ይዘው ወደ ንጉሡ ፊት መጡ።
25፤ ንጉሡም። ደኅነኛውን ሕፃን ለሁለት ከፍላችሁ ለአንዲቱ አንዱን ክፍል፥ ለሁለተኛይቱም ሁለተኛውን ክፍል ስጡ አለ።
26፤ ደኅነኛውም የነበራት ሴት አንጀትዋ ስለ ልጅዋ ናፍቆአልና። ጌታዬ ሆይ፥ ደኀነኛውን ለእርስዋ ስጣት እንጂ አትግደል ብላ ለንጉሡ ተናገረች። ያችኛይቱ ግን። ይከፈል እንጂ ለእኔም ለአንቺም አይሁን አለች።
27፤ ንጉሡም መልሶ። ይህችኛይቱ እናቱ ናትና ደኅነኛውን ሕፃን ለእርስዋ ስጡአት እንጂ አትግደሉት አለ።
28፤ ንጉሡም የፈረደውን ፍርድ እስራኤል ሁሉ ሰሙ፤ ፍርድን ለማድረግ የእግዚአብሔር ጥበብ እንደ ነበረበት አይተዋልና ንጉሡን ፈሩ።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  |  መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]