መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። - 2 Chronicles

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36

1፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮሳፍጥ ነገሠ፥ በእስራኤልም ላይ ጠነከረ።
2፤ በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ወታደሮችን አኖረ፥ በይሁዳም አገር አባቱም አሳ በወሰዳቸው በኤፍሬም ከተሞች ዘበኞችን አስቀመጠ።
3፤ እግዚአብሔርም ከኢዮሳፍጥ ጋር ነበረ፥ በፊተኛይቱ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄዶአልና፥ በኣሊምንም አልፈለገምና፤
4፤ ነገር ግን የአባቱን አምላክ ፈለገ፥ በትእዛዙም ሄደ፥ የእስራኤልንም ሥራ አልሠራም።
5፤ እግዚአብሔርም መንግሥቱን በእጁ አጸና፤ ይሁዳም ሁሉ እጅ መንሻ ለኢዮሳፍጥ አመጣ፤ እጅግም ብዙ ብልጥግናና ክብር ሆነለት።
6፤ ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ ከፍ ከፍ አለ፤ የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ ዐፀዱንም ከይሁዳ አስወገደ።
7፤ በነገሠም በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች ያስተምሩ ዘንድ መሳፍንቱን፥ ቤንኃይልን፥ አብድያስን፥ ዘካርያስን፥ ናትናኤልን፥ ሚክያስን፥ ሰደደ።
8፤ ከእነርሱም ጋር ሌዋውያንን ሸማያን፥ ነታንያን፥ ዝባድያን፥ አሣሄልን፥ ሰሚራሞትን፥ ዮናትንን፥ አዶንያስን፥ ጦብያን፥ ጦባዶንያን ሰደደ ከእነርሱም ጋር ካህናቱን ኤሊሳማንና ኢዮራምን ሰደደ።
9፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በይሁዳ ያስተምሩ ነበር፤ ወደ ይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሄደው ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር።
10፤ በይሁዳም ዙሪያ በነበሩ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድንጋጤ ሆነ፥ ከኢዮሳፍጥም ጋር አልተዋጉም።
11፤ ከፍልስጥኤማውያን ለኢዮሳፍጥ እጅ መንሻና የብር ግብር ያመጡ ነበር፤ ዓረባውያንም ደግሞ ከመንጎቻቸው ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ በጎችና ሰባት ሺህ ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ ፍየሎች ያመጡለት ነበር።
12፤ ኢዮሳፍጥም እየበረታና እጅግም እየከበረ ሄደ፤ በይሁዳም ግንቦችንና የጎተራ ከተሞችን ሠራ።
13፤ በይሁዳም ከተሞች ብዙ ሥራ ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም ጽኑዓን ኃያላን ሰልፈኞች ነበሩት።
14፤ ቍጥራቸውም እንደ አባቶቻቸው ቤት ይህ ነበረ፤ ከይሁዳ ሻለቆች አለቃው ዓድና፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤
15፤ ከእርሱም በኋላ አለቃው ይሆሐናን፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤
16፤ ከእርሱም በኋላ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የቀደሰ የዝክሪ ልጅ ዓማስያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ።
17፤ ከብንያምም ጽኑዕ ኃያል የነበረው ኤሊዳሄ፥ ከእርሱም ጋር ቀስትና ጋሻ የሚይዙ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤
18፤ ከእርሱም በኋላ ዮዛባት፥ ከእርሱም ጋር ለሰልፍ የተዘጋጁ መቶ ሰማኒያ ሺህ ሰዎች ነበሩ።
19፤ ንጉሡ በተመሸጉ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ካኖራቸውም ሌላ እነዚህ ንጉሡን ያገለግሉ ነበር።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]