መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። - 2 Chronicles

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36

1፤ ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ።
2፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ያለ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
3፤ አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ ለበኣሊምም መሠዊያ ሠራ፥ የማምለኪያ ዐፀዶችንም ተከለ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ፥ አመለካቸውም።
4፤ እግዚአብሔርም። ስሜ በኢየሩሳሌም ለዘላለም ይኖራል ባለው በእግዚአብሔር ቤት መሠዊያዎችን ሠራ።
5፤ በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ አደባባዮች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ።
6፤ በሄኖምም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ልጆቹን በእሳት አሳለፈ፤ ሞራ ገላጭም ሆነ፥ አስማትም አደረገ፥ መተተኛም ነበረ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ያስቈጣውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።
7፤8፤ እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን። በዚህ ቤት ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤ ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ በሙሴ የተሰጠውን ሕግና ሥርዓት ፍርድንም ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም፥ ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላርቅም ባለበት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሠራውን የጣዖት የተቀረጸውን ምስል አቆመ።
9፤ ምናሴም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳተ።
10፤ እግዚአብሔርም ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው፤ ግን አልሰሙትም።
11፤ ስለዚህም እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ ምናሴንም በዛንጅር ያዙት፥ በሰንሰለትም አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት።
12፤ በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን እግዚአብሔርን ፈለገ፥ በአባቶቹም አምላክ ፊት ሰውነቱን እጅግ አዋረደ፥
13፤ ወደ እርሱም ጸለየ፤ እርሱም ተለመነው፥ ጸሎቱንም ሰማው፥ ወደ መንግሥቱም ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው፤ ምናሴም እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ አወቀ።
14፤ ከዚህ በኋላ በዳዊት ከተማ በስተ ውጭው ከግዮን ምዕራብ በሸለቆው ውስጥ እስከ ዓሳ በር መግቢያ ድረስ ቅጥር ሠራ። በዖፌልም አዞረበት፥ እጅግም ከፍ አደረገው፤ በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጭፍራ አለቆችን አኖረ።
15፤ እንግዶችንም አማልክትና ጣዖቱንም ከእግዚአብሔር ቤት አራቀ፥ የእግዚአብሔርም ቤት ባለበት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ ወስዶ ከከተማይቱ በስተ ውጭ ጣላቸው።
16፤ የእግዚአብሔርንም መሠዊያ ደግሞ አደሰ፥ የደኅንነትና የምስጋናም መሥዋዕት ሠዋበት፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አዘዘ።
17፤ ሕዝቡ ግን ገና በኮረብታው መስገጃዎች ይሠዋ ነበር፤ ቢሆንም ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር።
18፤ የምናሴም የቀረው ነገር፥ ወደ አምላኩም የጸለየው ጸሎት፥ በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ስም የነገሩት የነቢያት ቃል፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።
19፤ ደግሞም ጸሎቱ፥ እግዚአብሔርም እንደ ተለመነው፥ ኃጢያቱና መተላለፉ ሁሉ፥ ራሱንም ሳያዋርድ የኮረብታው መስገጃዎችን የሠራበት የማምለኪያ ዐፀዱንና የተቀረጹትንም ምስሎች የተከለበት ስፍራ፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
20፤ ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቤቱም ቀበሩት፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
21፤ አሞጽ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ።
22፤ አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ አሞጽም አባቱ ምናሴ ለሠራቸው ለተቀረጹት ምስሎች ሁሉ ሠዋ፥ አመለካቸውም።
23፤ አባቱም ምናሴ ሰውነቱን እንዳዋረደ በእግዚአብሔር ፊት አንዳላዋረደ በእግዚአብሔርም ሰውነቱን አላዋረደም፤ ነገር ግን አሞጽ መተላለፉን እጅግ አበዛ።
24፤ ባሪያዎቹም ተማምለው በቤቱ ገደሉት።
25፤ የአገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ የተማማሉትን ሁሉ ገደሉ፤ የአገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡ።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]