መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። - 2 Chronicles

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36

1፤ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስም ቤት፥ ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ አሰበ።
2፤ ሰሎሞንም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ ከተራሮችም የሚጠርቡትን ሰማኒያ ሺህ፥ በእነርሱም ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ቈጠረ።
3፤ ሰሎሞንም እንዲህ ሲል ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ። ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ፥ የሚቀመጥበትንም ቤት ይሠራ ዘንድ የዝግባ እንጨት እንደ ሰደድህለት፥ እንዲሁ ለእኔ አድርግ።
4፤ እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘላለም እንደ ታዘዘው በእግዚአብሔር ፊት የጣፋጩን ሽቱ ለማጠን፥ የገጹንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም በመባቻዎቹም በአምላካችንም በእግዚአብሔር በዓላት ለማቅረብ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራና እቀድስ ዘንድ አሰብሁ።
5፤ አምላካችንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ታላቅ ነውና የምሠራው ቤት ታላቅ ነው።
6፤ ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ ይይዘው ዘንድ አይችልምና ለእርሱ ቤት ይሠራ ዘንድ ማን ይችላል? በፊቱ ዕጣን ከማጠን በቀር ቤት እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ?
7፤ አሁንም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው በእኔ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልሃተኞች ጋር የሚሆን፥ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ሐምራዊውንና ቀዩን ሰማያዊውንም ግምጃ የሚሠራ፥ ቅርጽንም የሚያውቅ ብልሃተኛ ሰው ላክልኝ።
8፤ ደግሞም ባሪያዎችህ ከሊባኖስ እንጨት መቍረጥ እንዲያውቁ እኔ አውቃለሁና ከሊባኖስ የዝግባና የጥድ የሰንደልም እንጨት ስደድልኝ።
9፤ የምሠራውም ቤት እጅግ ታላቅና ድንቅ ይሆናልና ብዙ እንጨት ያዘጋጁልኝ ዘንድ፥ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋር ይሆናሉ።
10፤ እነሆም፥ እንጨቱን ለሚቈርጡ ለባሪያዎችህ ሀያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተበጠረ ስንዴ፥ ሀያ ሺህም የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።
11፤ የጢሮስ ንጉሥም ኪራም። እግዚአብሔር ሕዝቡን ወድዶአልና በላያቸው አነገሠህ ብሎ ለሰሎሞን መልእክት ላከ።
12፤ ኪራምም ደግሞ አለ። ሰማይንና ምድርን የፈጠረ፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ ጥበበኛና ብልሃተኛ አስተዋይም ልጅ ለንጉሡ ለዳዊት የሰጠ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን።
13፤ አሁንም ከብልሃተኞችህ ጋር ከጌታዬም ከአባትህ ከዳዊት ብልሃተኞች ጋር ይሆን ዘንድ ኪራምአቢ የሚባል ብልሃተኛና አስተዋይ ሰው ሰድጄልሃለሁ።
14፤ እናቱ ከዳን ልጆች ናት፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ነው፤ ወርቁንና ብሩንም፥ ናሱንና ብረቱን፥ ድንጋይንና እንጨቱን፥ ሐምራዊውንና ሰማያዊውን ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ ይሠራ ዘንድ፥ ቅርጽም ሌላም ነገር ሁሉ ያደርግ ዘንድ ያውቃል።
15፤ አሁንም ጌታዬ የተናገረውን ስንዴውንና ገብሱን ዘይቱንና የወይን ጠጁን ወደ ባሪያዎቹ ይስደድ፤
16፤ እኛም ከሊባኖስ የምትሻውን ያህል እንጨት እንቈርጣለን፥ በታንኳም አድርገን በባሕር ላይ ወደ አንተ ወደ ኢዮጴ እንሰድዳለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ።
17፤ ሰሎሞንም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ አባቱ ዳዊት እንደ ቈጠራቸው ቈጠረ፤ መቶ አምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ተገኙ።
18፤ ከእነርሱም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ በተራሮችም ላይ የሚጠርቡትን ሰማንያ ሺህ፥ በሕዝቡም ሥራ ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ አደረገ።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  |  መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]