መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን - Songs of Solomon

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8

1፤ ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ዓይኖችሽ እንደ ርግቦች ናቸው፤ ጠጕርሽ በገለዓድ ተራራ እንደሚወርድ እንደ ፍየል መንጋ ነው።
2፤ ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ተሸለቱ ሁሉም መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው።
3፤ ከንፈሮችሽ እንደ ቀይ ሐር ፈትል ናቸው፥ አፍሽም ያማረ ነው፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ጕንጭና ጕንጭሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው።
4፤ አንገትሽ ለሰልፍ ዕቃ መስቀያ እንደ ተሠራው እንደ ዳዊት ግንብ ነው፤ ሺህ ጋሻ የኃያላንም መሣሪያ ሁሉ ተንጠልጥሎበታል።
5፤ ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ እንደ ተወለዱ፥ በሱፍ አበባ መካከል እንደሚሰማሩ እንደ ሚዳቋ ግልገሎች ናቸው።
6፤ ቀኑ እስኪነፍስ ጥላውም እስኪያልፍ ድረስ፥ ወደ ከርቤው ተራራ ወደ ዕጣኑም ኮረብታ እሄዳለሁ።
7፤ ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ነውርም የለብሽም።
8፤ ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከአማና ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ፥ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች።
9፤ እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ልቤን በደስታ አሳበድሽው፤ አንድ ጊዜ በዓይኖችሽ፥ ከአንገትሽ ድሪ በአንዱ ልቤን በደስታ አሳበድሽው።
10፤ እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ፍቅርሽ እንዴት መልካም ነው! ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ እንዴት ይሻላል! የዘይትሽም መዓዛ ከሽቱ ሁሉ!
11፤ ሙሽራዬ ሆይ፥ ከከንፈሮችሽ ማር ይንጠበጠባል፤ ከምላስሽ በታች ማርና ወተት አለ፥ የልብስሽም መዓዛ እንደ ሊባኖስ ሽታ ነው።
12፤ እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈ ገነት፥ የተዘጋ ምንጭ የታተመም ፈሳሽ ናት።
13፤ ቡቃያሽ ሮማንና የተመረጠ ፍሬ፥ ቆዕ ከናርዶስ ጋር ያለበት ገነት ነው፥
14፤ ናርዶስ ከቀጋ ጋር፥ የሽቱ ሣርና ቀረፋ፥ ከልዩ ልዩ ዕጣን ጋር፥ ከርቤና እሬት ከክቡር ሽቱ ሁሉ ጋር።
15፤ አንቺ የገነት ምንጭ፥ የሕይወት ውኃ ጕድጓድ፥ ከሊባኖስም የሚፈስስ ወንዝ ነሽ።
16፤ የሰሜን ነፋስ ሆይ፥ ተነሥ፥ የደቡብም ነፋስ ና፤ በገነቴ ላይ ንፈስ፥ ሽቱውም ይፍሰስ፤ ውዴ ወደ ገነቱ ይግባ፥ መልካሙንም ፍሬ ይብላ።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  |  መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]