መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን - Songs of Solomon

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8

1፤ አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ እንደ ወንድሜ ምነው በሆንህ! በሜዳ ባገኘሁህ ጊዜ በሳምሁህ፥ ማንም ባልናቀኝም ነበር።
2፤ መርቼ ወደ እናቴ ቤት ባገባሁህ፥ በዚያም አንተ ባስተማርከኝ፤ እኔም ከመልካሙ ወይን ጠጅ ከሮማኔም ውኃ ባጠጣሁህ ነበር።
3፤ ግራው ከራሴ በታች በሆነች ቀኙም ባቀፈችኝ ነበር።
4፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ ፍቅርን እንዳታስነሡት እንዳታነሣሡትም አምላችኋለሁ።
5፤ በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት? ከእንኮይ በታች አስነሣሁህ፤ በዚያ እናትህ ወለደችህ፥ በዚያም ወላጅ እናትህ አማጠችህ።
6፤ እንደ ማኅተም በልብህ፥ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና፥ ቅንዓትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና። ፍንጣሪዋ እንደ እሳት ፍንጣሪ፥ እንደ እግዚአብሔር ነበልባል ነው።
7፤ ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፥ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል።
8፤ እኛ ጡት የሌላት ታናሽ እኅት አለችን፤ ስለ እርስዋ በሚናገሩባት ቀን ለእኅታችን ምን እናድርግላት?
9፤ እርስዋ ቅጥር ብትሆን የብር ግንብ በላይዋ እንሠራለን፤ ደጅም ብትሆን በዝግባ ሳንቃ እንከብባታለን።
10፤ እኔ ቅጥር ነኝ ጡቶቼም እንደ ግንብ ናቸው፤ በዚያን ጊዜ በፊቱ ሰላምን እንደምታገኝ ሆንሁ።
11፤ ለሰሎሞን በብኤላሞን የወይን ቦታ ነበረው፤ የወይኑን ቦታ ለጠባቂዎች አከራየው፤ ሰው ሁሉ ለፍሬው ሺህ ብር ያመጣለት ነበር።
12፤ ለእኔ ያለኝ የወይን ቦታ በፊቴ ነው፤ ሰሎሞን ሆይ፥ ሺሁ ለአንተ፥ ሁለት መቶውም ፍሬውን ለሚጠብቁ ይሆናል።
13፤ በገነቱ የምትቀመጪ ሆይ፥ ባልንጀሮች የአንቺን ቃል ያደምጣሉ፤ ቃልሽን አሰሚኝ።
14፤ ውዴ ሆይ፥ ፍጠን፤ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ምሰል።

የገጽ ጫፍ  | የሚቀጥለው ምዕራፍ  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]