መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ሰቆቃው ኤርምያስ - Lamentations

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5

1፤ አሌፍ። ጌታ በቍጣው የጽዮንን ሴት ልጅ እንደ ምን አደመናት! የእስራኤልን ውበት ከሰማይ ወደ ምድር ጣለ፥ በቍጣውም ቀን የእግሩን መረገጫ አላሰበም።
2፤ ቤት። ጌታ የያዕቆብን ማደሪያዎች ሁሉ ዋጠ፥ አልራራምም፤ በመዓቱ የይሁዳን ሴት ልጅ አምቦች አፈረሰ፥ ወደ ምድርም አወረዳቸው፤ መንግሥቱንና አለቆችዋን አረከሰ።
3፤ ጋሜል። በጽኑ ቍጣው የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ቀጠቀጠ፤ ቀኝ እጁን ከጠላት ፊት ወደ ኋላ መለሰ፥ በዙሪያውም እንደሚባላ እንደ እሳት ነበልባል ያዕቆብን አቃጠለ።
4፤ ዳሌጥ። ቀስቱን እንደ ጠላት ገተረ፥ እንደ አስጨናቂ ቀኝ እጁን አጸና፥ ለዓይንም የሚያምረውን ሁሉ ገደለ፤ በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን መዓቱን እንደ እሳት አፈሰሰ።
5፤ ሄ። ጌታ እንደ ጠላት ሆነ፥ እስራኤልን ዋጠ፤ አዳራሾችዋን ሁሉ ዋጠ፥ አምቦችዋን አጠፋ፤ በይሁዳም ሴት ልጅ ኀዘንና ልቅሶ አበዛ።
6፤ ዋው። ማደሪያውን እንደ አትክልት ነቀለ፤ የበዓሉን ስፍራ አጠፋ፤ እግዚአብሔር በጽዮን ዓመት በዓሉንና ሰንበቱን አስረሳ፥ በቍጣውም መዓት ንጉሡንና ካህኑን አቃለለ።
7፤ ዛይ። ጌታ መሠዊያውን ጣለ፥ መቅደሱን ጠላ፥ የአዳራሾችዋንም ቅጥር በጠላት እጅ አሳልፎ ሰጠ፤ ድምፃቸውን እንደ ዓመት በዓል ቀን በእግዚአብሔር ቤት ከፍ ከፍ አደረጉ።
8፤ ሔት። እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ ቅጥር ያፈርስ ዘንድ አሰበ፤ የመለኪያውን ገመድ ዘረጋ፥ እጁን ከማጥፋት አልመለሰም፤ ምሽጉና ቅጥሩ እንዲያለቅሱ አደረገ፤ በአንድነት ደከሙ።
9፤ ጤት። በሮችዋ በመሬት ውስጥ ሰጠሙ፥ መወርወሪያዎችዋን አጠፋ ሰበረም፤ ንጉሥዋና አለቆችዋ ሕግ በሌለባቸው በአሕዛብ መካከል አሉ፤ ነቢያቶቻዋም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አላገኙም።
10፤ ዮድ። የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፤ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፤ የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ።
11፤ ካፍ። ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዓይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፤ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ።
12፤ ላሜድ። በከተማ ጐዳና እንደ ተወጋ ሰው በዛሉ ጊዜ፥ ነፍሳቸውም በእናቶቻቸው ብብት በወጣች ጊዜ፥ እናቶቻቸውን። እህልና የወይን ጠጅ ወዴት አለ? ይሉአቸዋል።
13፤ ሜም። የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፤ የሚፈውስሽ ማን ነው?
14፤ ኖን። ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል፤ ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም፤ ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል።
15፤ ሳምኬት። መንገድ አላፊዎች ሁሉ እጃቸውን ያጨበጭቡብሻልና። በውኑ የውበት ፍጻሜና የምድር ሁሉ ደስታ የሚሉአት ከተማ ይህች ናትን? እያሉ፥ በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያፍዋጫሉ፥ ራሳቸውንም ያነቃንቃሉ።
16፤ ዔ። ጠላቶችሽ ሁሉ አፋቸውን አላቀቁብሽ፤ እያፍዋጩና ጥርሳቸውን እያፋጩ። ውጠናታል፤ ነገር ግን ተስፋ ያደረግናት ቀን ይህች ናት፤ አግኝተናታል አይተናትማል ይላሉ።
17፤ ፌ። እግዚአብሔር ያሰበውን አደረገ፤ በቀድሞ ዘመን ያዘዘውን ቃል ፈጸመ፤ አፈረሰ አልራራምም፤ ጠላትንም ደስ አሰኘብሽ፥ የሚያስጨንቁሽንም ቀንድ ከፍ ከፍ አደረገ።
18፤ ጻዴ። ልባቸው ወደ ጌታ ጮኸ። የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፥ እንባሽን እንደ ፈሳሽ ቀንና ሌሊት አፍስሺ፤ ለሰውነትሽ ዕረፍት አትስጪ፤ የዓይንሽ ብሌን አታቋርጥ።
19፤ ቆፍ። ተነሺ፥ በሌሊት በመጀመሪያ ክፍል ጩኺ፥ በጌታም ፊት ልብሽን እንደ ውኃ አፍስሺ፤ በጐዳና ሁሉ ራስ ላይ በራብ ስለ ደከሙ ስለ ሕፃናትሽ ነፍስ እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ።
20፤ ሬስ። አቤቱ፥ እይ፤ በማን ላይ እንደዚህ እንዳደረግህ ተመልከት። በውኑ ሴቶች ፍሬያቸውን፥ ያቀማጠሉአቸውን ሕፃናት፥ ይበላሉን? በውኑ ካህኑና ነቢዩ በጌታ መቅደስ ውስጥ ይገደላሉን?
21፤ ሳን። ብላቴናውና ሽማግሌው በመንገዶች ላይ ተጋደሙ፤ ደናግሎቼና ጐበዛዝቴ በሰይፍ ወድቀዋል፤ በቍጣህ ቀን ገደልሃቸው፤ ሳትራራ አረድሃቸው።
22፤ ታው። እንደ በዓል ቀን የሚያስፈሩኝን ከዙሪያዬ ጠራህ፥ በእግዚአብሔር ቍጣ ቀንም ያመለጠ ወይም የቀረ አልተገኘም፤ ያቀማጠልኋቸውንና ያሳደግኋቸውን ጠላቴ በላቸው።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  |  መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]