መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ሰቆቃው ኤርምያስ - Lamentations
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
1
፤ አሌፍ። ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የመቅደሱ ድንጋዮች በጐዳና ሁሉ ራስ ተበተኑ።
2
፤ ቤት። ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ የጽዮን ልጆች፥ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቈጠሩ!
3
፤ ጋሜል። ቀበሮች እንኳ ጡቶታቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፤ የወገኔ ልጅ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጐን ጨካኝ ሆነች።
4
፤ ዳሌጥ። ጡት የሚጠባው የሕፃን ምላስ ከጥም የተነሣ ወደ ትናጋው ተጣበቀ፤ ሕፃናት እንጀራ ለመኑ፥ የሚቈርስላቸውም የለም።
5
፤ ሄ። የጣፈጠ ነገር ይበሉ የነበሩ በመንገድ ጠፉ፤ በቀይ ግምጃ ያድጉ የነበሩ የፍግ ክምር አቀፉ።
6
፤ ዋው። የማንም እጅ ሳይወድቅባት ድንገት ከተገለበጠች ከሰዶም ኃጢአት ይልቅ የወገኔ ሴት ልጅ ኃጢአት በዛች።
7
፤ ዛይ። አለቆችዋ ከበረዶ ይልቅ ጥሩ፥ ከወተት ይልቅ ነጭ ነበሩ፤ ገላቸው ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ቀይ ነበረ፥ መልካቸውም እንደ ሰንፔር ነበረ።
8
፤ ሔት። ፊታቸው ከጥቀርሻ ይልቅ ጠቍሮአል፥ በመንገድም አልታወቁም፤ ቁርበታቸው ወደ አጥንታቸው ተጣብቆአል፤ ደርቆአል፤ እንደ እንጨት ሆኖአል።
9
፤ ጤት። በሰይፍ የሞቱ በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፤ እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ቀጥነዋል።
10
፤ ዮድ። የርኅሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻችውን ቀቅለዋል፤ የወገኔ ሴት ልጅ በመቀጥቀጥዋ መብል ሆኑአቸው።
11
፤ ካፍ። እግዚአብሔር መዓቱን ፈጽሞአል፥ ጽኑ ቍጣውን አፍስሶአል፤ እሳትን በጽዮን ውስጥ አቃጠለ፥ መሠረትዋንም በላች።
12
፤ ላሜድ። የምድር ነገሥታት በዓለምም የሚኖሩ ሁሉ አስጨናቂና ጠላት በኢየሩሳሌም በር እንዲገባ አላመኑም።
13
፤ ሜም። የጻድቃንን ደም በውስጥዋ ስላፈሰሱ ስለ ነቢያቶችዋ ኃጢአትና ስለ ካህናቶች በደል ነው።
14
፤ ኖን። ታውረው በመንገድ ላይ ተቅበዘበዙ፤ ልብሳቸው እንዳይዳሰስ በደም ረክሰዋል።
15
፤ ሳምኬት። እናንተ ርኩሳን፥ ራቁ፥ ርቃችሁም ሂዱ፥ አትንኩ ብለው ጮኹባቸው። በሸሹና በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ በአሕዛብ መካከል። በዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖሩም ተባለ።
16
፤ ዔ። የእግዚአብሔር ፊት በተናቸው እርሱም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከታቸውም፤ የካህናቱን ፊት አላፈሩም፥ ሽማግሌዎቹንም አላከበሩም።
17
፤ ፌ። ዓይናችን ወደ ከንቱ ረዳታችን ገና ሲመለከት ጠፍቶአል፤ በመቆየታችን ማዳን የማይቻለውን ሕዝብ ጠብቀናል።
18
፤ ጻዴ። በአደባባያችን እንዳንሄድ ፍለጋችንን ተከተሉ፤ ፍጻሜያችን ቀርቦአል፥ ዕድሜያችን አልቆአል፥ ፍጻሜያችን ደርሶአል።
19
፤ ቆፍ። አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፥ በምድረ በዳ ሸመቁብን።
20
፤ ሬስ። ስለ እርሱ። በአሕዛብ መካከል በጥላው በሕይወት እንኖራለን ያልነው በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በጕድጓዳቸው ተያዘ።
21
፤ ሳን። በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ሐሤትም አድርጊ፤ ጽዋው ደግሞ ወደ አንቺ ያልፋል፥ አንቺም ትሰክሪአለሽ ትራቈቻለሽም።
22
፤ ታው። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የበደልሽ ቅጣት ተፈጸመ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አያስማርክሽም። የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ በደልሽን ይቀጣል፤ ኃጢአትሽን ይገልጣል።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]