መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ኦሪት ዘጸአት - Exodus

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40

1፤ በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።
2፤ ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ።
3፤ እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው፥
4፤ የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ።
5፤ ቀላያትም ከደኑአቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ።
6፤ አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ።
7፤ በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰድደህ፥ እንደ ገለባም በላቸው።
8፤ በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ።
9፤ ጠላትም። አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ።
10፤ ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ።
11፤ አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
12፤ ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው።
13፤ በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው።
14፤ አሕዛብ ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው።
15፤ የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞአብን ኃያላን መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ።
16፤ አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ በክንድህ ብርታት እንደ ድንጋይ ዝም አሉ።
17፤ አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፥ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፥ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ።
18፤ እግዚአብሔር ለዘላለሙ እስከ ፍጻሜ ይነግሣል።
19፤ የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕር ገቡ፥ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ ሄዱ።
20፤ የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ።
21፤ ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።
22፤ ሙሴም እስራኤልን ከኤርትራ ባሕር አስጓዘ፥ ወደ ሱርም ምድረ በዳ ወጡ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም።
23፤ ወደ ማራም በመጡ ጊዜ የማራ ውኃ መራራ ነበረና ሊጠጡ አልቻሉም፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም ማራ ተብሎ ተጠራ።
24፤ ሕዝቡም። ምን እንጠጣለን? ብለው በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ።
25፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤
26፤ እርሱም። አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና አለ።
27፤ እነርሱም ወደ ኤሊም መጡ፥ በዚያም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ነበሩባት፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]