መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ኦሪት ዘጸአት - Exodus

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40

1፤ በሦስተኛውም ወር የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ።
2፤ ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፥ በምድረ በዳም ሰፈሩ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈረ።
3፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በተራራው ጠርቶ አለው። ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር።
4፤ በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል።
5፤ አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤
6፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።
7፤ ሙሴም መጣ፥ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ።
8፤ ሕዝቡ ሁሉ አንድ አፍ ሆነው። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ እግዚአብሔር አደረሰ።
9፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ከአንተ ጋር ስነጋገር ሕዝቡ እንዲሰሙ፥ ደግሞም ለዘላለም እንዲያምኑብህ፥ እነሆ በከባድ ደመና እመጣልሃለሁ አለው። ሙሴም የሕዝቡን ቃል ለእግዚአብሔር ነገረ።
10፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ሕዝቡ ሂድ፥ ዛሬና ነገም ቀድሳቸው፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤
11፤ በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና ለሦስተኛው ቀን ይዘጋጁ።
12፤ ወሰንም ለሕዝቡ በዙሪያው አድርግላቸው። ወደ ተራራው እንዳትወጡ ጫፉንም እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ተራራውንም የነካ ፈጽሞ ይሞታል፤
13፤ የማንም እጅ አይንካ፤ ነገር ግን የሚነካው ሁሉ ይወገራል፥ ወይም በፍላጻ ይወጋል፤ እንስሳ ወይም ሰው ቢሆን አይድንም በላቸው። ሳያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በዚያን ጊዜ ወደ ተራራው ይውጡ።
14፤ ሙሴም ከተራራው ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ሕዝቡንም ቀደሰ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ።
15፤ ሕዝቡንም። ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ፥ ወደ ሴቶቻችሁ አትቅረቡ አለ።
16፤ እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ።
17፤ ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው፤ ከተራራውም እግርጌ ቆሙ።
18፤ እግዚአብሔርም በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር፤ ከእርሱም እንደ እቶን ጢስ ያለ ጢስ ይወጣ ነበር፥ ተራራውም ሁሉ እጅግ ይናወጥ ነበር።
19፤ የቀንደ መለከቱም ድምፅ እጅግ በበረታና በጸና ጊዜ ሙሴ ተናገረ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት።
20፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ወደ ተራራው ራስ ወረደ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ወደ ተራራው ራስ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።
21፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ውረድ፥ እግዚአብሔርን ለማየት ዳርቻውን እንዳያልፉ ከእነርሱም ብዙ እንዳይጠፉ ለሕዝቡ አስጠንቅቃቸው፤
22፤ ወደ እግዚአብሔርም የሚቀርቡት ካህናት ደግሞ እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ራሳቸውን ይቀድሱ አለው።
23፤ ሙሴም እግዚአብሔርን። አንተ። በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ ቀድሰውም ብለህ አስጠንቅቀኸናልና ሕዝቡ ወደ ተራራ ይወጡ ዘንድ አይችሉም አለው።
24፤ እግዚአብሔርም። ሂድ፥ ውረድ፤ አንተ አሮንም ከአንተ ጋር ትወጣላችሁ፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ወደ እግዚአብሔር ይወጡ ዘንድ አይተላለፉ አለው።
25፤ ሙሴም ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ይህንንም ነገራቸው።

የገጽ ጫፍ  |  | የሚቀጥለው ምዕራፍ |  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]