መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ኦሪት ዘጸአት - Exodus
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
15
16
17
18
19
20
21
22
23
24
25
26
27
28
29
30
31
32
33
34
35
36
37
38
39
40
1
፤ እኔንም በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርግባቸው ነገር ይህ ነው፤ ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ትወስዳለህ።
2
፤ ቂጣ እንጀራ፥ በዘይትም የተለወሰ የቂጣ እንጐቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ ከመልካም ስንዴ ታደርጋለህ።
3
፤ በአንድ ሌማትም ታደርጋቸዋለህ፤ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር በሌማቱ ታቀርባቸዋለህ።
4
፤ አሮንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ታቀርባቸዋለህ፥ በውኃም ታጥባቸዋለህ።
5
፤ ልብሶችን ወስደህ ለአሮን ሸሚዝና የኤፉድ ቀሚስ ኤፉድም የደረት ኪስም ታለብሰዋለህ፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቋድ ታስታጥቀዋለህ፤
6
፤ መጠምጠሚያውንም በራሱ ላይ ታደርጋለህ፥ የተቀደሰውንም አክሊል በመጠምጠሚያው ላይ ታኖራለህ።
7
፤ የቅብዓትንም ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ ታፈስሰዋለህ፥ ትቀባውማለህ።
8
፤ ልጆቹንም ታቀርባቸዋለህ፥ ሸሚዞቹንም ታለብሳቸዋለህ።
9
፤ አሮንንና ልጆቹንም በመታጠቂያ ታስታጥቃቸዋለህ፥ ቆብንም ታለብሳቸዋለህ፤ ለዘላለም ሥርዓትም ክህነት ይሆንላቸዋል፤ እንዲሁም አሮንንና ልጆቹን ትክናቸዋለህ።
10
፤ ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን በር ፊት ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናሉ።
11
፤ ወይፈኑንም በመገናኛው ድንኳን በር አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ታርደዋለህ።
12
፤ ከወይፈኑም ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣትህ ትረጨዋለህ፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ታፈስሰዋለህ።
13
፤ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ በጉልበቱም ላይ ያለውን መረብ ሁለቱንም ኵላሊቶች በላያቸውም ያለውን ስብ ወስደህ በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ።
14
፤ የወይፈኑን ሥጋ ግን፥ ቁርበቱንም፥ ፈርሱንም ከሰፈር ውጭ በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነው።
15
፤ አንደኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ።
16
፤ አውራውንም በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ።
17
፤ አውራውንም በግ በየብልቱ ትቈርጠዋለህ፥ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም ታጥባለህ፥ ከብልቱና ከራሱም ጋር ታኖረዋለህ።
18
፤ አውራውንም በግ በሞላው በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው፤ ጣፋጭ ሽቱ ነው። ለእግዚአብሔር የቀረበ የእሳት ቍርባን ነው።
19
፤ ሁለተኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በአውራው በግ ራስ ላይ ይጭናሉ።
20
፤ አውራውንም በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ትወስዳለህ፥ የአሮንንም የቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የልጆቹንም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ታስነካለህ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ።
21
፤ በመሠዊያውም ላይ ካለው ደም ከቅብዓት ዘይትም ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ ከእርሱም ጋር ባሉት በልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ትረጨዋለህ፤ እርሱም ልብሶቹም፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹ ልብሶቻቸውም ይቀደሳሉ።
22
፤ ደግሞም የሚካኑበት አውራ በግ ነውና የበጉን ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች በላያቸውም ያለውን ስብ፥ የቀኙንም ወርች ትወስዳለህ።
23
፤ አንድ እንጀራ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ በእግዚአብሔር ፊት በሌማት ካለው ቂጣ እንጀራ ትወስዳለህ፤
24
፤ ሁሉንም በአሮን እጆችና በልጆቹ እጆች ታኖረዋለህ፤ ለሚወዘወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትወዘውዘዋለህ።
25
፤ ከእጃቸውም ትቀበለዋለህ፥ በመሠዊያውም ላይ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በእግዚአብሔር ፊት ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን ታቃጥለዋለህ፤ እርሱ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነው።
26
፤ ለአሮንም ክህነት የታረደውን በግ ፍርምባ ወስደህ ለሚወዘወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትወዘውዘዋለህ፤ እርሱም የአንተ ወግ ይሆናል።
27
፤ ከሚካኑበትም አውራ በግ የተወሰደ ለአሮንና ለልጆቹ ወግ የሚሆን ለመሥዋዕት የተወዘወዘውን ፍርምባና የተነሣውን ወርች ትቀድሳለህ።
28
፤ ያውም የማንሣት ቍርባን ነውና ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ለዘላለም የአሮንና የልጆቹ ወግ ይሁን፤ የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡት የደኅንነት መሥዋዕታቸው የማንሣት ቍርባን ይሆናል፤ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ይሆናል።
29
፤ የተቀደሰውም የአሮን ልብስ ይቀቡበትና ይካኑበት ዘንድ ከእርሱ በኋላ ለልጆቹ ይሁን።
30
፤ ከልጆቹም በእርሱ ፋንታ ካህን የሚሆነው በመቅደስ ለማገልገል ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገባ ሰባት ቀን ይልበሰው።
31
፤ የሚካንበትንም አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ።
32
፤ አሮንና ልጆቹም የአውራውን በግ ሥጋ በሌማትም ያለውን እንጀራ በመገናኛው ድንኳን በር ይበሉታል።
33
፤ የተካኑና የተቀደሱ ይሆኑ ዘንድ ማስተስረያ የሆነውን ነገር ይብሉት፤ ሌላ ሰው ግን አይብላው፤ የተቀደሰ ነውና።
34
፤ የተካኑበትም ሥጋ ወይም እንጀራ ተርፎ ቢያድር፥ የቀረውን በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የተቀደሰ ነውና አይበላም።
35
፤ እንዳዘዝሁህም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ እንዲህ አድርግ፤ ሰባት ቀን ትክናቸዋለህ።
36
፤ ዕለት ዕለትም ስለ ማስተስረይ ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈኑን ታቀርባለህ፤ ማስተስረያም ባደረግህ ጊዜ መሠዊያውን ታነጻዋለህ፤ ቅዱስም ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ።
37
፤ ሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ ታደርጋለህ፥ ትቀድሰውማለህ፤ መሠዊያውም ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል፤ መሠዊያውንም የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።
38
፤ በመሠዊያውም ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ በቀን በቀን ዘወትር ሁለት የዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ።
39
፤ አንዱን ጠቦት በማለዳ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ፤ ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ።
40
፤ ከአንዱ ጠቦትም ጋር የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ደግሞ ለመጠጥ ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ።
41
፤ ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ታቀርበዋለህ፥ እንደ ማለዳውም የእህልና የመጠጥ ቍርባን ታደርግበታለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሆናል።
42
፤ ለአንተ እናገር ዘንድ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ፥ በእግዚአብሔር ፊት ይህ ዘወትር ለልጅ ልጃችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።
43
፤ ከእስራኤልም ልጆች ጋር በዚያ እገናኛለሁ፤ ድንኳኑም በክብሬ ይቀደሳል።
44
፤ የመገናኛውንም ድንኳን መሠዊያውንም እቀድሳለሁ፤ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ።
45
፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ አምላክም እሆናቸዋለሁ።
46
፤ በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው አምላካቸው እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝ።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]