መነሻ  |  | ድምጽ |  | ማውጫ |  | ምዕራፎች

ትንቢተ ሕዝቅኤል - Ezekiel

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48

1፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፤ ያዩ ዘንድ ዓይን አላቸው እነርሱም አያዩም፥ ይሰሙም ዘንድ ጆሮ አላቸው እነርሱም አይሰሙም፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።
3፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ እክት አዘጋጅ በፊታቸውም ቀን ለቀን ተማረክ፥ በፊታቸውም ከስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ተማርከህ ሂድ፤ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት እንደ ሆኑ ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል።
4፤ ቀን ለቀንም በፊታቸው እክትህን እንደ ስደተኛ እክት አውጣው፥ በማታም ጊዜ በፊታቸው ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ።
5፤ በፊታቸውም ግንቡን ንደል በእርሱም አውጣ።
6፤ ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና በፊታቸው በጫንቃህ ላይ አንግተው፥ በጨለማም ተሸክመህ ውጣ፤ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን።
7፤ እንዳዘዘኝም አደረግሁ፤ ቀን ለቀንም እክቱን እንደ ስደተኛ እክት አወጣሁ፥ በማታም ጊዜ ግንቡን በእጄ ነደልሁ፥ በጨለማም አወጣሁት በፊታቸውም በጫንቃዬ ላይ አንግቼ ተሸከምሁት።
8፤ በነጋውም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
9፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ዓመፀኛ ቤት የእስራኤል ቤት። የምታደርገው ምንድር ነው? አላሉህምን?
10፤ አንተም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ሸክም በኢየሩሳሌም በሚኖረው አለቃ ላይ በመካከላቸውም በሚኖሩት በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ ነው በላቸው።
11፤ ደግሞም። እኔ ምልክታችሁ ነኝ፤ እኔ እንዳደረግሁ እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱም በስደት ወደ ምርኮ ይሄዳሉ በል።
12፤ በመካከላቸውም የሚኖረው አለቃ በጫንቃው ላይ አንግቶ በጨለማ ይወጣል፤ በዚያ ያወጡ ዘንድ ግንቡን ይነድላሉ፥ በዓይኑም ምድርን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል።
13፤ መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ከለዳውያንም ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ሆኖም አያያትም በዚያም ይሞታል።
14፤ ሊረዱትም በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ጭፍሮቹንም ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ።
15፤ በአሕዛብም መካከል በበተንኋቸው ጊዜ፥ በአገሮችም በዘራኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
16፤ በሚሄዱባቸውም አሕዛብ መካከል ርኵሰታቸውን ሁሉ ይናገሩ ዘንድ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም ጥቂቶች ሰዎችን ከእነርሱ አስቀራለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
17፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እንጀራህን በድንጋጤ ብላ ውኃህንም በመንቀጥቀጥና በኀዘን ጠጣ፤
19፤ ለምድሪቱም ሕዝብ። ጌታ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩ ስለ እስራኤልም ምድር እንዲህ ይላል። ስለሚኖሩባት ሁሉ ግፍ ምድሪቱ ከነሞላዋ ትጠፋ ዘንድ እንጀራቸውን በችግር ይበላሉ ወኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ።
20፤ ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ባድማ ይሆናሉ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው።
21፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
22፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር። ዘመኑ ረዝሞአል ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል የምትሉት ምሳሌ ምንድር ነው?
23፤ ስለዚህ እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፤ አንተ ግን። ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቦአል በላቸው።
24፤ ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም።
25፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እናገራለሁ የምናገረውም ቃል ይፈጸማል፥ ደግሞም አይዘገይም፤ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
26፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
27፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የእስራኤል ቤት። ይህች የሚያያት ራእይ ለብዙ ዘመን ናት፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል ይላሉ።
28፤ ስለዚህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል እግዚአብሔር።

የገጽ ጫፍ  | የሚቀጥለው ምዕራፍ  | ማውጫ  | መነሻ
Full online version here [with search engine, multilingual display and audio Bible]