መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ትንቢተ ሕዝቅኤል - Ezekiel
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
15
16
17
18
19
20
21
22
23
24
25
26
27
28
29
30
31
32
33
34
35
36
37
38
39
40
41
42
43
44
45
46
47
48
1
፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2
፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ርኵሰትዋን አስታውቃት፥
3
፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላል። ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ ነበረ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች።
4
፤ በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቈረጠም ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨውም አልተቀባሽም በጨርቅም አልተጠቀለልሽም።
5
፤ በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጕስቍልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዓይን አልራራልሽም፥ ማንም አላዘነልሽም።
6
፤ በአንቺም ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ በደምሽም ውስጥ ተለውሰሽ ባየሁሽ ጊዜ። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፤ አዎን። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ።
7
፤ በእርሻ ላይ እንዳለ ቡቃያ አበዛሁሽ፥ አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በእጅጉም አጌጥሽ፤ ጡቶችሽም አጐጠጐጡ ጠጕርሽም አደገ፥ ነገር ግን ዕርቃንሽን ሆንሽ፥ ተራቍተሽም ነበርሽ።
8
፤ በአንቺ ዘንድ ባለፍሁና ባየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበረ፤ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ዘረጋሁ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም ለእኔ ሆንሽ።
9
፤ በውኃም አጠብሁሽ ከደምሽም አጠራሁሽ በዘይትም ቀባሁሽ።
10
፤ ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ በአቆስጣ ቁርበትም ጫማ አደረግሁልሽ፤ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ በሐርም ከደንሁሽ።
11
፤ በጌጥም አስጌጥሁሽ በእጅሽም ላይ አንባር በአንገትሽም ላይ ድሪ አደረግሁልሽ።
12
፤ በአፍንጫሽም ቀለበት በጆሮሽም ጕትቻ በራስሽም ላይ የክብር አክሊል አደረግሁ።
13
፤ በወርቅና በብር አጌጥሽ፥ ልብስሽም ጥሩ በፍታና ሐር ወርቀ ዘቦም ነበረ፤ አንቺም መልካምን ዱቄትና ማርን ዘይትንም በላሽ፤ እጅግ በጣም ውብ ሆንሽ ለመንግሥትም ደረስሽ።
14
፤ ባንቺ ላይ ካኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15
፤ ነገር ግን በውበትሽ ታምነሻል ስለ ዝናሽም አመንዝረሻል ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ።
16
፤ ከልብስሽም ወስደሽ በኮረብቶች ላይ በዝንጕርጕር ልብስ ያስጌጥሻቸውን መስገጆች ለራስሽ ሠራሽ በዚያም ገለሞትሽ፤ እንዲህም ያለ ነገር ከአሁን በፊት አልነበረም፥ ከእንግዲህም ወዲያ አይሆንም።
17
፤ ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አድርገሻል አመንዝረሽባቸውማል።
18
፤ ወርቀዘቦውን ልብስሽንም ወስደሽ ደረብሽላቸው፥ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አኖርሽ።
19
፤ የሰጠሁሽንም እንጀራዬን ያበላሁሽንም መልካሙን ዱቄትና ዘይቱን ማሩንም ጣፋጭ ሽታ አድርገሽ በፊታቸው አኖርሽ፥ እንዲሁም ሆኖአል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
20
፤ ለእኔም የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ወስደሽ መብል ይሆኑ ዘንድ ሠዋሽላቸው።
21
፤ ልጆቼን አረድሽ፤ ለእነርሱም በእሳት በኩል አሳልፈሽ ሰጠሽ፤ በውኑ ግልሙትናሽ ጥቂት ነውን?
22
፤ በርኵስነትሽና በግልሙትናሽ ሁሉ ዕርቃንሽን ሆነሽ ተራቍተሽም ሳለሽ በደምሽም ተለውሰሽ ሳለሽ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽም።
23
፤ ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤
24
፤ ከክፋትሽም ሁሉ በኋላ የምንዝርናን ስፍራ፥ በየአደባባዩም ከፍ ያለ ቦታን ለራስሽ ሠራሽ።
25
፤ በየመንገዱ ራስ ከፍ ያለውን ቦታሽን ሠራሽ፥ ውበትሽንም አረከስሽ፥ ለመንገድ አላፊም ሁሉ እግርሽን ገለጥሽ ግልሙትናሽንም አበዛሽ።
26
፤ ሥጋቸውም ከወፈረ ከጐረቤቶችሽ ከግብጻውያን ጋር አመነዘርሽ፥ እኔንም ታስቈጭ ዘንድ ግልሙትናሽን አበዛሽ።
27
፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቻለሁ ድርጐሽንም አጕድያለሁ፤ ለሚጠሉሽም ከክፉ መንገድሽ የተነሣ ለሚያፍሩ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች ፈቃድ አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ።
28
፤ አልጠገብሽምና ከአሦራውያን ጋር ደግሞ ገለሞትሽ ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም።
29
፤ እስከ ነጋዴዎች ምድር እስከ ከላውዴዎን ድረስ ግልሙትናሽን አበዛሽ። ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም።
30
፤ የማታፍረውን የጋለሞታን ሥራ ሁሉ ሠርተሻልና ልብሽ ምንኛ ደካማ ነው? ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
31
፤ በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል በየአደባባዩም ከፍ ያለውን ቦታሽን አድርገሻል። ዋጋዋን እንደምትንቅ እንደ ጋለሞታ አልሆንሽም።
32
፤ በባልዋ ፋንታ ሌሎችን ተቀብላ የምታመነዝር ሴትን ትመስያለሽ።
33
፤ ለጋለሞቶች ሁሉ ዋጋ ይሰጡአቸዋል፤ አንቺ ግን ለውሽሞችሽ ሁሉ ዋጋ ትሰጫለሽ፥ ከአንቺም ጋር ለማመንዘር በዙሪያሽ ይገቡብሽ ዘንድ መማለጃ ትሰጫቸዋለሽ።
34
፤ ግልሙትናሽ ከሌሎች ሴቶች ግልብጥ ነው፤ ማንም ለግልሙትና የሚከተልሽ የለም፤ ዋጋ ሳይሰጥሽ አንቺ ዋጋ በመስጠትሽ በዚህ ነገር ልዩ ሆነሻል።
35
፤ ስለዚህ፥ ጋለሞታ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ።
36
፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከውሽሞችሽ ጋር ባደረግሽው በግልሙትናሽ ርኵሰትሽ ስለ ፈሰሰ ኀፍረተ ሥጋሽም ስለ ተገለጠ፥ ስለ ርኵሰትሽም ጣዖታት ሁሉ ስለ ሰጠሻቸውም ስለ ልጆች ደም፥
37
፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ ከእነርሱ ጋር ደስ ያለሽን የወደድሻቸውንም ውሽሞችሽ ሁሉ ከጠላሻቸው ሁሉ ጋር እሰበስባቸዋለሁ፤ በአንቺ ላይ በዙሪያሽ እሰበስባቸዋለሁ፥ ኀፍረተ ሥጋሽንም ሁሉ እንዲያዩ በፊታቸው ኀፍረተ ሥጋሽን እገልጣለሁ።
38
፤ በአመንዝሮችና በደም አፍሳሾች ላይ የሚፈረደውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፥ የመዓትንና የቅንዓትን ደምም አመጣብሻለሁ።
39
፤ በእጃቸውም አሳልፌ እሰጥሻለሁ፥ የምንዝርናሽንም ስፍራ ያፈርሳሉ ከፍ ያለውንም ቦታሽን ይገለብጣሉ፤ ልብስሽንም ይገፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ፥ ዕርቃንሽን አድርገው ዕራቁትሽን ይተዉሻል።
40
፤ ጉባኤን ያመጡብሻል በድንጋይም ይወግሩሻል፥ በሰይፋቸውም ይወጉሻል።
41
፤ ቤቶችሽንም በእሳት ያቃጥላሉ በብዙም ሴቶች ፊት በላይሽ ፍርድን ያደርጉብሻል፤ ግልሙትናሽንም አስተውሻለሁ፥ እንግዲህስ ዋጋ አትሰጭም።
42
፤ መዓቴንም በአንቺ ላይ እጨርሳለሁ ቅንዓቴም ከአንቺ ይርቃል፥ እኔም ዝም እላለሁ ደግሞም አልቈጣም።
43
፤ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽምና፥ በዚህም ነገር ሁሉ አስቈጥተሽኛልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ ደግሞ መንገድሽን በራስሽ ላይ አመጣለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ሌላንም ነውር በርኵሰትሽ ሁሉ ላይ አትጨምሪም።
44
፤ እነሆ፥ በምሳሌ የሚናገር ሁሉ። እንደ እናቲቱ እንዲሁ ሴት ልጂቱ ናት እያለ ምሳሌ ይመስልብሻል።
45
፤ አንቺ ባልዋንና ልጆችዋን የጠላሽ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የጠሉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ፤ እናታችሁ ኬጢያዊት ነበረች አባታችሁም አሞራዊ ነበረ።
46
፤ ታላቂቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ግራሽ የምትቀመጥ ሰማርያ ናት፤ ታናሺቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ቀኝሽ የምትቀመጥ ሰዶም ናት።
47
፤ አንቺ ግን በመንገዳቸው አልሄድሽም እንደ ርኵሰታቸውም አላደረግሽም ያው ለአንቺ ጥቂት ነበረና በመንገድሽ ሁሉ ከእነርሱ የሚከፋ ርኵሰት አደረግሽ።
48
፤ እኔ ሕያው ነኝና አንቺና ሴቶች ልጆችሽ እንዳደረጋችሁት እንዲሁ ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ አላደረጉም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
49
፤ እነሆ፥ የእኅትሽ የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፤ ትዕቢት እንጀራን መጥገብ መዝለልና ሥራ መፍታት በእርስዋና በሴቶች ልጆችዋ ነበረ፥ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም።
50
፤ ኰርተው ነበር በፊቴም ርኩስ ነገር አደረጉ፤ ስለዚህ ባየሁ ጊዜ አጠፋኋቸው።
51
፤ ሰማርያም የኃጢአትሽን እኵሌታ አልሠራችም፤ አንቺ ግን ከእኅቶችሽ ይልቅ ርኵሰትሽን አበዛሽ፥ በሥራሽም ርኵሰት ሁሉ አጸደቅሻቸው።
52
፤ አሁንም ለእኅቶችሽ ስለ ፈረድሽ እፍረትሽን ተሸከሚ፤ ከእነርሱ የባሰ ኃጢአት ሠርተሻልና ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ናቸው፤ እኅቶችሽንም ስለ አጸደቅሻቸው እፈሪ እፍረትሽንም ተሸከሚ።
53
፤ ምርኮአቸውን፥ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋንም ምርኮ፥ በመካከላቸውም ያሉትን የምርኮኞችሽን ምርኮ እመልሳለሁ፤
54
፤ ስለ አጽናናሻቸው፥ እፍረትን ትሸከሚ ዘንድ ስለ አደረግሽውም ሁሉ ታፍሪ ዘንድ።
55
፤ እኅቶችሽም ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ ሰማርያና ሴቶች ልጆችዋም ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ አንቺና ሴቶች ልጆችሽም ወደ ቀድሞ ሁኔታችሁ ትመለሳላችሁ።
56
፤ ክፋትሽ ሳይገለጥ በትዕቢትሽ ቀን እኅትሽ ሰዶም በአፍሽ መተረቻ አልነበረችምን?
57
፤ አሁን ለሶርያ ሴቶች ልጆችና ለጎረቤቶችዋ ሁሉ፥ በዙሪያሽም ለሚንቁሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች እንደ እርስዋ መሰደቢያ ሆነሻል።
58
፤ ምንዝርነትሽንና ርኵስነትሽን ተሸክመሻል፥ ይላል እግዚአብሔር።
59
፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። አንቺ ቃል ኪዳንን በማፍረስ መሐላን የናቅሽ ሆይ፥ አንቺ እንዳደረግሽ እኔ ደግሞ አደርግብሻለሁ።
60
፤ ነገር ግን በሕፃንነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ የዘላለምንም ቃል ኪዳን አጸናልሻለሁ።
61
፤ እኅቶችሽንም ታላቂቱንና ታናሺቱን በተቀበልሽ ጊዜ መንገድሽን ታስቢያለሽ ታፍሪማለሽ፤ ለአንቺም ልጆች ይሆኑ ዘንድ እሰጣቸዋለሁ፥ ስለ ቃል ኪዳንሽ ግን አይደለም።
62
፤
63
፤ ስላደረግሽውም ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፥ ታስቢ ዘንድ ታፍሪም ዘንድ ስለ እፍረትሽም ደግሞ አፍሽን እንዳትከፍቺ፥ ቃል ኪዳኔን ከአንቺ ጋር አጸናለሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]