መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ትንቢተ ሕዝቅኤል - Ezekiel
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
15
16
17
18
19
20
21
22
23
24
25
26
27
28
29
30
31
32
33
34
35
36
37
38
39
40
41
42
43
44
45
46
47
48
1
፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2
፤ አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርዳለህን? ደም በምታፈስስ ከተማ ላይ ትፈርዳለህን? ርኵሰትዋን ሁሉ አስታውቃት።
3
፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጊዜሽ እንዲደርስ በመካከልሽ ደምን የምታፈስሺ እንድትረክሺም በራስሽ ላይ ጣዖታትን የምታደርጊ ከተማ ሆይ!
4
፤ ባፈሰስሽው ደም በድለሻል ባደረግሽውም ጣዖታት ረክሰሻል፤ ቀንሽን አቀረብሽ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፤ ስለዚህ ለአሕዛብ መሰደቢያ ለአገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ።
5
፤ አንቺ ስምሽ የረከሰ ሽብርም የሞላብሽ ሆይ፥ ወደ አንቺ የቀረቡና ከአንቺ የራቁ ይሳለቁብሻል።
6
፤ እነሆ፥ የእስራኤል አለቆች እያንዳንዱ እንደ ችሎቱ ደም ያፈስሱ ዘንድ በአንቺ ውስጥ ነበሩ።
7
፤ በአንቺ ውስጥ አባትንና እናትን አቃለሉ፤ በመካከልሽ በመጻተኛው ላይ በደልን አደረጉ፤ በአንቺ ውስጥ ድሀ አደጉንና መበለቲቱን አስጨነቁ።
8
፤ ቅድሳቴንም ናቅሽ ሰንበታቴንም አረከስሽ።
9
፤ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ቀማኞች ሰዎች በአንቺ ውስጥ ነበሩ፤ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ በሉ፤ በመካከልሽ ሴሰኝነትን አደረጉ።
10
፤ በአንቺ ውስጥ የአባቶቻቸውን ኀፍረተ ሥጋ ገለጡ፤ በአንቺም ውስጥ አደፍ ያለባትን አዋረዱ።
11
፤ ሰውም በባልንጀራው ሚስት ርኵሰትን አደረገ፥ አባትም የልጁን ሚስት አረከሰ፥ በአንቺም ዘንድ ወንድም የአባቱን ልጅ እኅቱን አሳፈረ።
12
፤ በአንቺ ውስጥ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ጉቦን ተቀበሉ፤ አንቺም አራጣና ትርፍ ወስደሻል፥ ከባልንጀሮችሽም በቅሚያ የስስትን ትርፍ አገኘሽ፥ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
13
፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ አንቺ ባደረግሽው ስስት በመካከልሽም በነበረው ደም ላይ እጄን አጨበጨብሁ።
14
፤ በውኑ እኔ በማደርግብሽ ወራት ልብሽ ይታገሣልን? ወይስ እጅሽ ትጸናለችን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ አደርገውማለሁ።
15
፤ ወደ አሕዛብም እበትንሻለሁ ወደ አገሮችም እዘራሻለሁ፥ ርኵሰትሽንም ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ።
16
፤ በአሕዛብም ፊት አንቺ ትረክሻለሽ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂአለሽ።
17
፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18
፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ለእኔ እንደ አተላ ሆኑብኝ፤ እነርሱ ሁሉ በከውር ውስጥ መዳብና ቈርቈሮ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ የብር አተላ ናቸው።
19
፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁላችሁ አተላ ሆናችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰበስባችኋለሁ።
20
፤ እንዲያቀልጡት እሳት ያናፉበት ዘንድ ብርንና መዳብን ብረትንና እርሳስን ቈርቈሮንም በከውር እንደሚሰበስቡ፥ እንዲሁ በቍጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፥ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ አቀልጣችሁማለሁ።
21
፤ አሰበስባችሁማለሁ የመዓቴንም እሳት አናፋባችኋለሁ በውስጡም ትቀልጣላችሁ።
22
፤ ብርም በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በውስጡዋ ትቀልጣላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ።
23
፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
24
፤ የሰው ልጅ ሆይ። አንቺ ያልነጻሽ በቍጣም ቀን ያልዘነበብሽ ምድር ነሽ በላት።
25
፤ በውስጥዋ ያሉ ነቢያት እንደሚጮኽና እንደሚናጠቅ አንበሳ አንድ ሆነው ተማማሉ፤ ነፍሶችን በልተዋል፥ ብልጥግናና ሀብትን ወስደዋል፥ በውስጥዋም መበለቶችን አብዝተዋል።
26
፤ ካህናቶችዋም ሕጌን በድለዋል ቅድሳቴንም አርክሰዋል፤ ቅዱስ በሆነና ቅዱስ ባልሆነ መካከልም አልለዩም፥ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውን ልዩነት አላስታወቁም፤ ዓይናቸውንም ከሰንበታቴ ሰወሩ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ።
27
፤ በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኵላዎች ናቸው።
28
፤ እግዚአብሔርም ሳይናገር ነቢያቶችዋ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ከንቱን ራእይ በማየት የሐሰትንም ምዋርት ለእነርሱ በማምዋረት ያለ ገለባ በጭቃ ይመርጓቸዋል።
29
፤ የምድርን ሕዝብ ግፍ አደረጉ ቅሚያም ሠሩ፤ ድሆችንና ችግረኞችን አስጨነቁ፥ መጻተኛውንም በደሉ።
30
፤ ቅጥርን የሚጠግንን፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው በመካከላቸው ፈለግሁ፥ ነገር ግን አላገኘሁም።
31
፤ ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]