መነሻ
| |
ድምጽ
| |
ማውጫ
| |
ምዕራፎች
ትንቢተ ሕዝቅኤል - Ezekiel
ምዕራፍ:
1
2
3
4
5
6
7
8
9
10
11
12
13
14
15
16
17
18
19
20
21
22
23
24
25
26
27
28
29
30
31
32
33
34
35
36
37
38
39
40
41
42
43
44
45
46
47
48
1
፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2
፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በጎግ ላይና በማጎግ ምድር ላይ፥ በሞሳሕና በቶቤል ዋነኛ አለቃ ላይ አቅናበት፥ ትንቢትም ተናገርበት፥
3
፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሞሳሕና የቶቢል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ።
4
፤ እመልስህማለሁ በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ፥ አንተንና ሠራዊትህንም ሁሉ፥ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን የጦር ልብስ የለበሱትን ሁሉ፥ ጋሻና ራስ ቍርን ሰይፍንም ያያዙትን ሁሉ፥ ታላቁን ወገን አወጣለሁ፥
5
፤ ፋርስንና ኢትዮጵያን ፉጥንም ከእነርሱ ጋር ጋሻና የራስ ቍርን የለበሱትን ሁሉ፥
6
፤ ጋሜርንና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ በሰሜን ዳርቻም ያለውን የቴርጋማን ቤትና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ ብዙዎችንም ሕዝቦች ከአንተ ጋር አወጣለሁ።
7
፤ አንተና ወደ አንተ የተሰበሰቡ ወገኖችህ ሁሉ ተዘጋጁ፥ አንተም ራስህን አዘጋጅተህ አለቃ ሁናቸው።
8
፤ ከብዙ ዘመንም በኋላ ትፈለጋለህ፤ በኋለኛውም ዘመን፥ የዘላለም ባድማ በነበሩ በእስራኤል ተራሮች ላይ ከብዙ ሕዝብ ውስጥ ወደ ተሰበሰበች፥ ከሰይፍ ወደ ተመለሰች ምድር ትገባለህ፤ እርስዋም ከሕዝብ ውስጥ ወጥታለች ሁሉም ሳይፈሩ ይቀመጡባታል።
9
፤ አንተም ትወጣለህ፥ እንደ ዐወሎ ነፋስም ትመጣለህ፤ አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ምድርን እንደ ደመና ትሸፍናላችሁ።
10
፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይገባል፥
11
፤ ክፉ አሳብንም ታስባለህ፥ እንዲህም ትላለህ። ቅጥርን ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ፤ ተዘልለው ወደሚኖሩ፥ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡ እገባለሁ፤
12
፤ ምርኮን ትማርክ ዘንድ ብዝበዛንም ትበዘብዝ ዘንድ፥ ባድማም በነበሩ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፥ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፥ ከብትና ዕቃንም ባገኘ፥ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ።
13
፤ ሳባና ድዳን የተርሴስም ነጋዴዎች መንደሮችዋም ሁሉ። ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን? ይሉሃል።
14
፤ አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለዚህ ትንቢት ተናገር ጎግንም እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል ሳይፈራ በተቀመጠ ጊዜ አንተ አታውቀውምን?
15
፤ አንተም፥ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ሁላቸው በፈረሶች ላይ የተቀመጡ፥ ታላቅ ወገንና ብርቱ ሠራዊት፥ ከሰሜን ዳርቻ ከስፍራችሁ ትመጣላችሁ።
16
፤ ምድርንም ትሸፍን ዘንድ እንደ ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። በኋለኛው ዘመን ይሆናል፥ ጎግ ሆይ፥ በዓይናቸው ፊት በተቀደስሁብህ ጊዜ አሕዛብ ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።
17
፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ በዚያች ዘመን ብዙ ዓመት ትንቢት በተናገሩ በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያቶች በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን?
18
፤ በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ መቅሠፍቴ በመዓቴ ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
19
፤ በቅንዓቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ። በእርግጥ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤
20
፤ ከፊቴም የተነሣ የባሕር ዓሣዎችና የሰማይ ወፎች የምድረ በዳም አራዊት በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ በምድርም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፥ ተራሮችም ይገለባበጣሉ ገደላገደሎችም ይወድቃሉ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል።
21
፤ በተራሮቼም ሁሉ በእርሱ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
22
፤ በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍም የበረዶም ድንጋይ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ።
23
፤ ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
የገጽ ጫፍ
| |
የሚቀጥለው ምዕራፍ
| |
ማውጫ
|
መነሻ
Full online version
here
[with search engine, multilingual display and audio Bible]